በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን በሙህር አክሊል ወረዳ የመጠጥ ውሃ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ተጣለ።

በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን በሙህር አክሊል ወረዳ የመጠጥ ውሃ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ተጣለ።

ሰኔ 19/2016ዓ.ም(ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ በኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰምድር ውሃ ፕሮጀክት አካል የሆነው በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን የሙህር አክሊል ወረዳ የመቆርቆር ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የመሠረት ድንጋይ ተጣለ።፡

የመሰረት ድንጋዩን ያስቀመጡት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ የወረዳው የዘመናት ጥያቄ የሆነውን የመቆርቆር የውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የተገኙትን በማመስገን ለሠው ልጅ አስፈላጊና ህይወት የሆነን የውሃ ሀብት መጠበቅ፣ መንከባከብና ማልማት ተገቢ መሆኑን ጠቁመው ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀከት በኢትዮጵያ ሲተገበር በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታላሚ ያደረገ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ መተግበር ከተጀመረ 2አመታት አስቆጥሯል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በዚሁ ጊዜ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እንዲተገበር በተቀመጠው መሠረት ትኩረት ተሠጥቶ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፍላጎትን ለማሟላት በርካታ ስራዎች ተሠርተዋል ብለዋል።

በተለያዩ ክልሎች የመሠረት ድንጋይ ስናስቀምጥ ከአመራር ጀምሮ እስከ ተጠቃሚው ከእያንዳንዳችን የሚጠበቀውን በመወጣት የሚገጥሙ ችግሮችን በቅንጅትና በትብብር መንፈስ በመፍታት የህብረተሰቡን የረጅም ጊዜ ጥያቄ በአጭር ጊዜ በመፍታት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ሲሉ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አደራ ሰጥተዋል።

ይህን ፕሮጀክት በታለመው ልክ ተግባራዊ ማድረግ እንደ ሀገር ተጨማሪ በጀት ለማግኘት ወሳኝ በመሆኑ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ክትትል አለበት ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ዛሬ የመሠረት ድንጋይ ሲጣል ነገ ግንባታው መጀመር እንዳለበት ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት እንዳለበትና ኮንትራክተሩም በአጭር ጊዜ ፕሮጀክቱን አጠናቆ ለተጠቃሚው እንዲደርስ ሙሉ እምነት እንደተጣለበት ገልጸዋል።

በሚቀጥሉት 5 እና 6 አመታትም በተቻለ መጠን ህብረተሰቡን በንጹህ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ ከምን ጊዜውም በላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራልም ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አቶ ላጫ ጋሩማ እንዳሉት ዞኑ በርካታ የገጸ ምድርና ከርሰ ምድር የውሃ ክምችት ያለው በመሆኑ በዘርፉ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፉ ህዝባችን በሚጠበቀው ልክ ተጠቃሚ ሆኗል ማለት አይቻልም ብለዋል።

ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የህብረተሠቡን ችግር ተረድቶ የ ወረዳውን ሶስት ቀበሌዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የፕሮጀክት ማስጀመሪያ የመሠረት ድንጋይ መጣሉ በእጅጉ በማመስገን ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ 38 በመቶ የነበረውን የዞን የውሃ ሽፋን ወደ 46 በመቶ ከፍ ያደርገዋል ብለዋል።

በፕሮጀክቱም 13 ሺ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑና 57ሚሊየን ብር ወጭ እንደሚደረግበት ገልጸዋል።

የውሃ መስኖና ማእድን ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ዳዊት ሀይሉ የምሁር አክሊል ወረዳ በዞኑ ውሃ አጠር ከሆኑና የውሃ ሽፋናቸው ዝቅተኛ ከሆኑ ወረዳዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ችግሩን ተረድቶ እድሉን ስለሠጠ በእጅጉ ሊመሠገን ይገባል ብለዋል።

የውሃን ችግር መፍታት አጠቃላይ የመልካም አስተዳደርን ችግሮ ለመፍታት መሠረት ነው ያሉት ሀላፊው ለችግሩ አንገብጋቢነት ሚኒስትቴር መስሪያ ቤቱ የሠጠው ምላሽ በእጅጉ ተገቢ ነው ብለዋል።

የውሃ ግንባታ ከሌሎች ግንባታዎች በተለየ ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ የሚጠይቅ በመሆኑ ተቋራጮች በፍጥነት በማጠናቀቅ ፣ ህብረተሰቡም የሚጠበቅበትን በመወጣት በፕሮጀክት መጓተት የሚከሰተውን ችግር ከወዲሁ መከላከል እንዲቻል ሲሉም አሳስበዋል።

በመርሃ ግብሩ ክቡር ዶ/ር አብርሃ አዱኛን ጨምሮ የሚኒስትሪው ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልል ፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች፣ የሀይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች የተገኙ ሲሆን የአካባቢው ማህበረሰብም የፕሮጀክቱን ማስጀመር አስመልክቶ ደስታቸውን በተለያዩ መንገዶች አንጸባርቀዋል።

Share this Post