’’ግድቤን በደጄ ’’ በሚል መሪቃል የተጀመረው የዝናብ ውሃን ከጣራ የማሰባሰብና ጥቅም ላይ የማዋል ተግባር ውጤታማ መሆኑ ተገለጸ፡፡

‘‘ግድቤን በደጀ (Dam at My Yard)’’ በሚል መሪቃል የተጀመረው የዝናብ ውሃን ከጣራ የማሰባሰብና ጥቅም ላይ የማዋል ተግባር ውጤታማ መሆኑ ተገለጸ፡፡ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አነሳሽነት ግድቤን በደጀ (Dam at My Yard) በሚል መሪቃል በኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ግቢ ውስጥ በፓይለት ፕሮጀክት ደረጃ የተጀመረው የጣራ ላይ ውሃ የማሰባሰብ ስራ ውጤታማ መሆኑ ተገለጸ፡፡ በቦረና ዞን በሚገኙ ትምህርት ቤቶችና መንደሮች እየተተገበሩ የሚገኙ የውሃ ማሰባሰብ ፕሮጀክቶች ጉብኝት በተደረገበት ወቅት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ እንደገለጹት በቀላል ወጪ የሚተገበሩ ቴክኖሎጂዎችን የማመንጨትና የመደገፍ ተግባርን መሠረት በማድረግ በኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት በፓይለት ደረጃ ተሰርቶ ውጤታማነቱ ተረጋግጦ ወደ ማህበረሰቡ መውረዱን ገልጸው፤ ከዚህ በፊት በተለምዶ ውሃ ማቆር በመባል ከሚታወቀው የውሃ መያዝ ተግባር የሚለየው ከጣራ ንጹህ ውሃ የመሰብሰብና በተገቢው ሁኔታ በማጣራት ለልዩ ልዩ አገልግሎቶች እንዲውል ማደረጉ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ውሃውን ለመሳብ ጥቅም ላይ የሚውሉት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች መኖራቸውን አስታውሰዋል ፡፡ ክቡር ሚኒስቴሩ አክለውም የውሃ እጥረት ባለባቸውና በድርቅ ተጠቂ ለሆኑ አካባቢዎች፤ በቦረና፣ በሶማሌ፣ በቤንሻጉል እንዲሁም በአማራ ክልል እንደሚስፋፋ ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ እንደገለጹት፤ ቴክኖሎጂው ቀላልና የዝናብ ውሃን በቀላሉ በመሰብሰብ ለልዩ ልዩ ግልጋሎት ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑን አውስተው፤ በግለሰብ ደረጃ ሊተገብር የሚችል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ክቡር ሚኒስቴር ዴኤታው አክለውም፤ በአካባቢው ‘‘ኤላ’’ በመባል የሚታወቅ ቀደምት አባቶችና እናቶች በባህላዊ መንገድ ውሃን የመያዝ ተግባር የነበረ መሆኑንና ይህ ቴክኖሎጂ በዘመናዊ መንገድ መምጣቱን ገልጸው፤ ይህን ቴክኖሎጂ ለማስፋፋት ሰፊ ስራ እንደሚጠይቅ አስታውሰዋል፡፡ በጉብኝቱ ወቅት ማብራሪያ የሰጡት የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ታመነ ሀይሉ በበለኩላቸው የጣራ ላይ ውሃ ማሰባሰብ ተግባር በኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ግቢ ውስጥ በፓይለት ፕሮጀክት ደረጃ በመተግበር አዋጭነቱን ከተረጋገጠ በኋላ በቦረና በተመረጡ ትምህርት ቤቶች እየተተገበረ መገኘቱነ ገልጸዋል፡፡ በየትምህርት ቤቶች እየተተገበረ የሚገኘው የጣራ ውሃ ማሰባሰብ ፕሮጀክት የትምህርት ሚኒስቴር ያወጣውን እስታንዳርድ መሰረት በማድረግ መሆኑን ገልጸው፤ የጣራ ውሃ የማሰባሰብና ለልዩ ልዩ አገልግሎቶች እንዲውል ታሳቢ በማድረግ በትምህትርት ቤቶች መተግበር የተጀመረበት ዋነኛ ምክንያት በውሃ እጥረት ምክንያት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንዳይለዩ የማድረግ ዓላማን በማንገብ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ውሃው ከተከማቸ በኋላ ውሃውን አውጥቶ ለመጠቀም ሰባት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ ይገኛል፡፡ እየተተገበሩ ለሚገኙት ፕሮጀክቶች የሶላር ፓምፕና ትሪድል ፓምፕ ውሃውን ለማውጣት ጥቅም ላይ የዋሉ ሲሆን፤ በቀጣይ ውሃውን ለማጣራት ያሉትን በርካታ አማራጮች ላይ የማስተማርና የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡ የዝናብ ውሃ የማሰባሰብ ሂደቱ ጂኦሜምብሬን፣ ቆርቆሮ፣ ሚስማር፤ ሶላር፤ ትሪድል ፓምፕና የመሳሰሉት ገብዓቶች ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ በቦረና ዞን በስምንት ትምህርት ቤቶች ለመተግበር የተጀመረ ሲሆን በአራቱ ትምህርት ቤቶች በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡

Share this Post