የኢትዮጵያ ጎርፍ መከላከል ፕሮጀክትን ውጤታማ ለማድረግ ማህበራዊና አካባቢያዊ ደህንነትን ማስጠበቅ ላይ ትኩረት ያደረገ ስልጠና እየተሰጠ ነው።
የኢትዮጵያ ጎርፍ መከላከል ፕሮጀክትን ውጤታማ ለማድረግ ማህበራዊና አካባቢያዊ ደህንነትን ማስጠበቅ ላይ ትኩረት ያደረገ ስልጠና እየተሰጠ ነው።
ግንቦት /2016ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ጎርፍ መከላከል ፕሮጀክትን ውጤታማ ለማድረግ ማህበራዊና አካባቢያዊ ደህንነትን ማስጠበቅ ላይ ትኩረት ያደረገ ስልጠና ለማህበራዊና አካባቢያዊ ባለሙያዎች እንዲሁም ለሚመለከታቸው አካላት በአዳማ እየተሰጠ ይገኛል ።
በስልጠናው ማስጀመሪያ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ ጎርፍ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአለም ስጋት እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰው ችግሩን ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት ባይቻልም ስጋቱን መቀነስ የሚያስችል የጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት ወደ ተግባር ገብቷል ብለዋል።
ከአሁን በፊት አዋሽ ተፋሰስ ላይ የጎርፍ ስጋት ችግሮችን ለመቀነስ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል ያሉት አማካሪው አጠናክሮ ከማስቀጠል አኳያ የተወሠኑ ክፍቶች ይስተዋሉ እንደነበር እና ፕሮጀክቱ ክፍተቶችን በመለየት ከአለም ባንክ በተገኘ የ300 ሚሊዬን ዶላር ድጋፍ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሚቲዎሮሎጂ ፣ከአደጋ ስጋት ና መከላከል ኮሚሽን ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ፕሮግራሙ የተቀረጸው ለአምስት ዓመታት መሆኑን የገለጹት አማካሪው እስካሁን በነበረው የፕሮጀክት አፈጻጸም ሂደት ምክንያታዊ በሆኑ ጉዳዮች ያልተተገበሩ ስራዎችን በቀጣይ አራት አመታት በተለይም አዋሽ፣ ሰምጥ ሸለቆና ኦሞ ተፋሰሶች ላይ ትኩረት አድርጎ በርካታ ስራዎችን መስራት የግድ መሆኑን አበክረው ተናግረዋል።
አክለውም ከተቋማት ጀምሮ እስከ አማካሪ ባለው የአፈጻጸም ሂደት ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበትና ማህበራዊና አካባቢያዊ ተጽኖዎችን መከላከል ላይ ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ መሆኑ ታውቆ ስልጠናውን በአግባቡ በመከታተል መሬት ላይ ለሚሰራው ስራ ስንቅ የሚሆን ነገር መጨበጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት ኮርድኔተር ኢ/ር ተመስገን ከተማ እንዳሉት ጎርፍ የሚያደርሰውን አደጋ ለመቀነስ በተቀረጸው ፕሮጀክት ከአለም ባንክ እንደ አስገዳጅ ቁልፍ ነጥብ ሆነው የተቀመጡ ሁኔታዎችን በማሟላት የጎርፍ አደጋ ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች ላይ የዳሰሳ ጥናት ፣ የዲዛይን ጥናትና የአዋጭነት ጥናት በማካሄድ አስፈላጊ መዋቅራዊ አደረጃጀቶች ተሰርተው ቅድሚያ የሚሰጣቸው ተፋሠሶችን በመለየት እገዛ ማድረግን ያካተተ ሪፖርት በማቅረብ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ በሶስት ዋና ዋና ተፋሰሶች ላይ ወደ ትግበራ ተገብቷል ብለዋል።
በፕሮጀክቱ የአንድ ዓመት የትግበራ ሂደትም የተለያዩ ስራዎች ማለትም ከግዥ ጋር የተያያዙ፣ የአቅም ግንባታ እና ሌሎች ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የገለጹት አስተባባሪው እንደነዚህ አይነት የስልጠናና ውይይት መድረኮች ተፋሰሶች ምን ላይ እንዳሉ ከማወቅ ባለፈ ውጤታማ ስራ ለመስራት ጠቀሜታቸው የጎላ ነው ብለዋል።
የፕሮጀክቱ የአካባቢያዊ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሰለሞን ሀይለኢየሱስ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በሚተገበርባቸው ተፋሰሶች ሊደርስ የሚችለውን ማህበራዊና አካባቢያዊ ተጽእኖ ቀድሞ በመለየት ማስወገድ ባይቻል እንኳን መቀነስ የሚቻልበትን የማስተካከያ ርምጃዎችን በማቀድ ጉዳት ሳይደርስ ለመከላከል ሰልጣኞች የተግባር ልምምድን ያካተተ ስልጠና መውሰዳቸው አቅማቸውን በማጎልበት መሬት ላይ ለሚሰራው ስራ በእጅጉ ያግዛቸዋል ብለዋል።
ስልጠናውን የወሰዱ በክልልና በወረዳ ደረጃ ያሉ የሚመለከታቸው ሀላፊዎች፣ የአካባቢያዊና ማህበራዊ ባለሙያዎች እንዲሁም በየደረጃው ያሉ ፎካል ፐርሰኖች ስራዎችን ወደ መሬት ሲያወርዱ ተገቢ የሆነ አካባቢያዊና ማህበራዊ ተጽእኖ ግምገማ በማድረግ ፣ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ውይይትና ምክክር በማካሄድ ሀላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በስልጠናው ከቤዚን አስተዳደር ጽ/ቤቶች፣ ከክልል ውሃና ኢነርጂ እና መስኖና ቆላማ ቢሮዎች፣ ከፌደራል የአካባቢ ጥበቃ፣ ከከተማ መሠረተ ልማት ሚኒስቴር እንዲሁም ከሚቲዎሮሎጂ ኢንስትቲዩት እና ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተውጣጡ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ሲሆን ስልጠናው ለቀጣይ 4ቀናት የሚቀጥል ይሆናል።