በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ እየተገናበ የሚገኘው የባዮጋዝ ማብላያ ፕሮጀክት ተጎበኘ፡፡

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ እየተገናበ የሚገኘው የባዮጋዝ ማብላያ ፕሮጀክት ተጎበኘ፡፡

ሚያዝያ 08/2016 ዓ.ም.(ው.ኢ.ሚ) በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ እየተገነባ የሚገኘው በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ 300 ሜትር ኪዩብ የባዮጋዝ ማብላያ ፕሮጀክት ተጎበኘ፡፡

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ የተመራ ቡድን በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የሚገነባውን የባዮጋዝ ማብላያ ፕሮጀክት ያለበትን ደረጃ ጎብኝተዋል።

ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በጉብኝቱ ወቅት እንደገለፁት ፕሮጀክቱ እንደሀገር የመጀመሪያና ዲዛይኑም የተለየ፤ ህብረተሰቡን የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችልና ተሞክሮውን በማስፋትና ተማሪዎችንም ስለኃይል ማመንጫ ምንነት ለማስተማር ትልቅ ሚና እንዳለው ገልፀው ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ አሳስበዋል።

ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም እንደሀገር የባዮጋዝ ቴክኖሎጂን ማስፋፋት አዋጭ ቢሆንም፤ በቤተሰብ ደረጃ እንጂ በተቋም ደረጃ ያልተተገበረ እንደነበር ገልጸው፤ መንግስት ሴክተሩን እየደገፈ እንደመሆኑ ህብረተሰቡ በራሱ አቅም ከባለሙያዎችና ከተቋማት ጋር በመቀናጀት ፕሮጀክቱን መደገፍ አለበት ብለዋል።

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ የትምህርት ክፍል አባልና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ አሸናፊ አበበ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የዩኒቨርስቲውን ተረፈምርት መነሻ በማድረግ ግንባታው ከUNDP በተገኘ 263 ሺ ዶላር ድጋፍ በተያዘው ዓመት እንደተጀመረና ዩኒቨርሲቲውም ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀው ኮንትራቱን የወሰደው የቻይና ድርጅት ቴክኒካል ስራዎችን ካጠናቀቀ በሚቀጥሉት ወራቶች አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ገልፀዋል።

የክልሉን የኃይል ፍላጎት ላይ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል ያሉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የኢነርጂ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኦላዶ ኦሎ ለተቋሙና ለአካባቢው ህብረተሰብ ችግር ፈቺ ፕሮጀክት በመሆኑ ወደሌላ ዩኒቨርስቲዎችና ትላልቅ ተቋማት ተሞክሮውን ማስፋት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ቡድኑ ከጉብኝቱ በኃላ ከዩኒቨርስቲው አመራሮች፣ ከፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች፣ ከቻይና ድርጅት ተወካዮችና ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር በቀሪ ስራዎች ዙሪያ ውይይት አድርገው የቀጣይ ስራዎችን አቅጣጫ ላይ በጋራ እንደሚሰሩ መክረዋል።

Share this Post