የብሔራዊ ዋሽ ፕሮግራም ማኔጅመንት ዩኒት የዘጠኝ ወር አፈጻጸም ተገመገመ።

የብሔራዊ ዋሽ ፕሮግራም ማኔጅመንት ዩኒት የዘጠኝ ወር አፈጻጸም ተገመገመ።

ሚያዚያ 6/2016 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የብሔራዊ ዋሽ ፕሮግራም ማኔጅመንት ዩኒት (National WaSH Program Management Unit) ዩኒት የዘጠኝ ወር አፈጻጸምን በአዳማ አዩ ሆቴል ባዘጋጀው መድረክ ገምግሟል።

በመድረኩ የክልሎች አፈጻጸም ቀርቦ በስፋት ውይይት ተደርጎበታል።

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የዋን ዋሽ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ተስፋየ ሉሌ ፐሮግራሙ እንደ ሀገር በ50 ከተሞች በ308 ወረዳዎች እና በ42 የሲአር ዋሽ ወረዳዎች የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት ተደራሽ የሚደረግበት በመሆኑ በክፍል ደረጃ በየጊዜው እየተገመገመ መመራቱ አፈጻጸማችን በማሻሻል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያግዛል ብለዋል።

መድረኩ ቅድሚያ ትኩረት አድርገን የምንፈጽማቸውን ተግባራት የለየንበት ነው ያሉት አስተባባሪው፤ በክልሎች ያለውን የአፈጻጸም ግምገማ መነሻ በማድረግ ቅድሚያ ትኩረት የሚሹትን በመለየት የፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም ውጤታማ እንዲሆን የጋራ አቅጣጫ ያስቀመጥንበት ሲሉ ገልጸውታል።

በቀጣይም ውይይቱን በማጠናከር የፕሮግራሙን ውጤታማነት ለማረጋገጥ ይሰራልም ብለዋል።

በፕሮግራሙ አተገባበር የተሻለ ውጤት የተመዘገበበት የአማራ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ የዋን ዋሽ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ አስራት ካሳየ በሰጡን አስተያየት አፈጻጸማቸውን የተሻለ ያደረገው ከአማካሪ፣ ኮንትራክተርና አሰሪ ተቋማት ጋር በየወሩ በሚያደርጉት ውይይት ችግሮችን ከመሠረቱ እየፈቱ በመስራታቸው እና የህብረተሠቡን ተሳትፎ በማጠናከር እንደሆነ ተናግረዋል።

ምንም እንኳን በክልሉ የጸጥታ ስጋት ቢኖርም የሙያተኛው፣ የአመራሩና የህብረተሰቡ ለለልማቱ ያለው ቁርጠኝነት ከፍተኛ በመሆኑ እስካሁን በተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች 225ሺ የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

መድረኩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በለውጥ ጎዳና ላይ እንዳለ ማሳያ ነው ያሉት አስተባባሪው ክፍተታችን በመለየት፣ ልምድ በመለዋወጥና የጋራ አቅጣጫ በማስቀመጥ ለተሻለ ውጤት የምንበቃበትን እድል የፈጠረ ነው ሲሉም ገልጸውታል።

የትግራይ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ የዋን ዋሽ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዳኛው ሀጎስ በበኩላቸው ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ከክልል እስከ ወረዳ በተዘረጋው መዋቅር ስልጠና በመስጠት ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸው 72ሺ የህብረተሰብ ክፍልን በፕሮግራሙ ተጠቃሚ ለማድረግ በሚያደርጉት ጥረት ህብረተሰቡ መሬት በነጻ ከመስጠት ጀምሮ በተለያዩ ተሳትፎዎች ከጎናቸው በመሆኑም ውጤታማ ስራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

መድረኩ በዘርፉ ለረጅም አመት በማገልገል አስተዋጽኦ ያበረከቱ ባለሙያዎችን እውቅና በመስጠት ተጠናቋል።

Share this Post