የኢነርጂ ሀብቶችን ፈጣን እና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ በማልማት ተደራሽነትን ለማስፋት የሚያስችል ዘላቂ የሀይል ልማት ስትራቴጂ ይፋ ተደረገ፡፡

የኢነርጂ ሀብቶችን ፈጣን እና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ በማልማት ተደራሽነትን ለማስፋት የሚያስችል ዘላቂ የሀይል ልማት ስትራቴጂ ይፋ ተደረገ፡፡

ሚያዚያ 4/2016 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ሀብቶችን ፈጣን እና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ በማልማት ተደራሽነትን ለማስፋት የሚያስችል ዘላቂ የሀይል ልማት ስትራቴጂ አዲስ አበባ ሀይሌ ግራንድ ባካሄደው አውደ ጥናት ይፋ አደረገ፡፡

በእለቱ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ በሰጡት ቃለ ምልልስ የኢነርጂ ፖሊሲው የግል ባለሀብቱን ተሳታፊነት የሚያጠናከር መሆኑን ጠቅሰው የፖሊሲውን አፈጻጸም ለማሳለጥና የግሉን ዘርፍ በልማቱ ተሳታፊ ለማድረግ አስፈላጊ የሆነ ስትራቴጂ ነው ብለዋል፡፡

ስትራቴጂው ሲቀረጽ መንግስት ካስቀመጣቸው በርካታ ጉዳዮች ጋር እንዲናበብ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው፤ በአብዛኛው ለነዳጅ ፍጆታ የሚውለውን የመንግስት ወጭ በኤሌክትሪክ ሀይል የመተካት ስራን የሚደግፍ በመሆኑ የውጭ ምንዛሬን በመቀነስ ረገድ የሚያበረክተው አስተጽኦ ከፍተኛ እንደሆነና የሚፈለገው ኢነርጂ በተፈለገው ጊዜ፣ ፍጥነትና ቦታ እንዲውል አዋጭና ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ማቅረብንም ግምት ውስጥ ያስገባ ነው ብለዋል፡፡

ሀገራችን ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት ላይ መሆኗን የገለጹት ክቡር ሚኒስተር ዴኤታው የሀይል ዘርፉን ውጤታማነት በመንግስት አቅም ብቻ ማሳካት ስለማይቻል የግል ሴክተሩ በሀይል ማመንጨት፣ ማስተላለፍ እና ማሰራጨት ተግባሩ ላይ ተሳታፊ እንዲሆን ስትራቴጂው እድል ይሰጣል ብለዋል፡፡

አክለውም የስትራቴጂው ዋና ግብ የሀገራችን የኢነርጂ ሀብት ፈጣንና ቀጣይነት እንዲኖረው በስፋት ፍትሃዊና ተደራሽ በሆነ መልኩ በማልማት ለዜጎች ተደራሽ እንዲሆን ብሎም የሀገር ውስጥ ኢኮኖሚን በመደገፍ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል፤ በቀጣይም ከሚመለከታቸው ሴክተሮች ጋር ስትራቴጅው በጋራ ይተገበራል ብለዋል፡፡

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኢነርጂ ሀብት ጥናት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ካሌብ ታደሰ በበኩላቸው 60 ሚሊየን የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ከኤሌክትሪክ መስመር ውጭ እንደሚኖር፣ 90 በመቶ የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ ንጹህ የማብሰያ ቴክኖሎጅዎችን እንደማይጠቀሙና ለተለያዩ የጤና እክሎች እየተዳረጉ መሆናቸውን፣ የኢነርጂ አቅርቦት ላይም ተመርቶ ከተጠቃሚው አስኪደርስ ድረስ በብዙ እንደሚባክን ጠቅሰው ስትራቴጂው የኢነርጂ ስብጥርን በማሳደግ፣ አቅርቦትን በማሻሻል፣ ብክነትን በመቀነስ፣ የግል ሴክተሩን በማሳተፍና የኢነርጂ አስተዳደርና አቅም ግንባታ ላይ ትኩረት የማድረግ አላማን እውን ያደርጋል ብለዋል፡፡

በእለቱ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ ሃላፊዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች፣ አጋር የልማት ድርጅቶች፣ የሚመለከታቸው የፌደራል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ የክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮዎችና የግሉ ዘርፍ ተሳታፊ ነበሩ፡፡

Share this Post