ግድቤን በደጄ ፕሮጀክት ላይ ስልጠና እየተሰጠ ነው።

ግድቤን በደጄ ፕሮጀክት ላይ ስልጠና እየተሰጠ ነው።

መጋቢት 17/2016ዓ.ም( ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን የዝናብ ውሃ የማሰባሠብ እና ጥቅም ላይ ለማዋል በተቀረጸው የግድቤን በደጄ ፕሮጀክት በመስኩ ለተደራጁ እና ከተለያዩ ክልሎች ለመጡ ማህበራት በአርባ ምንጭ ከተማ ስልጠና እየተሰጠ ነው።

በስልጠናው መጀመሪያ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የክቡር ሚኒስትሩ የኮሙኒኬሽን አማካሪ ወ/ሮ ገበያነሽ ነጋሽ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ንጹህ የመጠጥ ውሃን ተደራሽ ለማድረግ በመጠጥ ውሃና በውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፎች በርካታ ስራዎቾ እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሰው ውሃ አላቂ ሀብት በመሆኑ በእንክብካቤ፣ በቁጠባና በንጽህና ይዘን እያለማን መጠቀም አለብን ብለዋል።

እንደ አማካሪዋ ገለጻ የዝናብ ውሃን በማሠባሠብ ጥቅም ላይ የማዋል የግድቤን በደጄ ፕሮጀክት ከአሁን በፊት በተጠና መልኩ በቦረናና በጎንደር ተሞክሮ ውጤታማ ሆኗል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በክረምት ወቅት ከፍተኛ መጠን ያለው የዝናብ ውሃ የምታገኝበት እድሉ ሰፊ ነው የሚሉት አማካሪዋ ጎርፍ እየሆነ የሚያልፈውንና አልፎ አልፎም አደጋ የሚያስከትለውን ውሃ በመያዝ በበጋ ወቅት ዝናብ አጠር የሆኑ አካባቢዎች ውሃን የሚያገኙበት እድልን በመፍጠር ፣ ለበርካታ ዜጎች መፍትሔ በመሆንና ለወጣቶችም የስራ እድል በመፍጠር አስተዋጽኦ የሚያበረክት ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

አክለውም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመሆን በቀጣይነት በፕሮጀክቱ የታቀፉ አካባቢዎችን የውሃ ችግር ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት እና የተጀመረውን ፕሮጀክት ውጤታማ ለማድረግ የስልጠና መድረኩ አንዱ ምዕራፍ ነው ብለዋል።

በእለቱ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ ዶ/ር ሚካኤል መሃሪ በውሃ አሰባሰብ ጽንሰ ሀሳብና ሂደቱ ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል።

ስልጠናው ለተከታታይ 3 ቀናት የሚሰጥ ሲሆን በተመሳሳይ በድሬዳዋና ሻሸመኔ ከተሞች በዘርፉ ከፍተኛ ባለሙያዎች እየተሰጠ ይገኛል።

Share this Post