የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን መሬት ላይ ለማውረድ የተፋሰስ እቅድ አንዱ መሳሪያ ነው ተባለ።

የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን መሬት ላይ ለማውረድ የተፋሰስ እቅድ አንዱ መሳሪያ ነው ተባለ።

መጋቢት 9/2019ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን መሬት ላይ ለማውረድ ወሳኝ የሆነውና በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ እየተዘጋጀ ያለውን የባሮ አኮቦ የተፋሰስ እቅድ ዝግጅትን በሚመለከት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቶበታል።

በውይይቱ መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር አብርሃ አዱኛ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደ ሀገር ያሉትን የወንዝና ሀይቅ የውሃ ሀብቶች በሚገባ ለመምራት የተፋሰስ እቅድ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው ብዙ ያልተጠቀምንበት

፣ በርካታ ሀብት ያለው ፣ ለአባይ ተፋሰስ ገባር የሆነና በርካታ ወንዞች በዙሪያው ያሉትን የባሮ አኮቦ ተፋሰስ ላይ የተፋሰስ እቅድ ለማዘጋጀት ከደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር በ2014ዓ.ም በጋራ የሚሰራበት ስምምነት ተደርጎ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደ ሀገር የሚያስበውን የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን ለማስፈን የተፋሰስ እቅድ አንዱ ስትራቴጅክ መረጃ ተደርጎ ተወስዷል ብለዋል።

የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን መሬት ላይ ለማውረድ የተፋሰስ እቅድ አንዱ መሳሪያ ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በተፋሰስ ውስጥ ያሉትን ሀብቶች ለልማት ለማዋል ያስችል ዘንድ ሁሉም አካላት በጋራ የሚያቅዱበትና በጋራ ሪፖርታቸውን የሚገመግሙበት እንዲሁም አንድ እቅድ አንድ ሪፖርት በሚል መርህ የተፋሰሱን ሀብት በጋራ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚቻልበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየተዘጋጀ ያለ እቅድ ነው ብለዋል።

የተፋሰስ እቅዱ ላይ ከዝግጅት ምእራፍ ጀምሮ ከተለያዩ የጉዳዩ ባለቤቶች ጋር ውይይት መደረጉን የገለጹት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ውይይቱ ባለድርሻዎች የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ምቹ ሁኔታን በማመቻቸት ፣ ችግሮችን የጋራ በማድረግ እና የተገኘውን ሀሳብና አስተያየት በመቀመር ከችግሩ ለመውጣት እንደጥሩ መደላድል የሚወሰድበትን እድል የፈጠረ ነው ብለዋል።

አክለውም መሬት ላይ ያለውን ችግር ታሳቢ በማድረግ የተፋሰስ እቅዱን ለማጎልበት በሚያስችል መልኩ በሚቀርበው የተፋሰስ እቅድ የሁኔታ ግምገማ (Situation Assessment) ሁላችንም በንቃት በመሳተፍ የተሠሩትን ስራዎች በደንብ ለማጎልበት፣ የሚቀሩትን ለማስተካከል እድል የሚሰጥ በመሆኑና በውሃ ሀብቱ ላይ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራትን ጥቅም ሳንነካ የሀገራችን ጥቅም ለማስከበር በጋራ የሚፈለግብንን ሙያዊ አስተዋጽኦ እንድናበረክት ከዛም ባሻገር ችግሩን በጋራ አይተን ቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫ የምናስቀምጥበትን የጋራ አላማ ያነገበ መድረክ ነው ብለዋል።

የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ክቡር ዶ/ር ለታ ተስፋየ እንዳሉት የባሮ አኮቦ የተፋሰስ እቅድ ጽንሰ ሀሳብ ዙሪያ ከተመራማሪዎች ጋር ውይይት በማድረግ ስራው እንደተጀመረ ገልጸው ከፌደራል እና ከክልል ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች መረጃ ተሠብስቦ፣መሬት ላይ ያለውን ሀብትና ችግሮችን በመለየት የመስክ ምልከታ በማድረግ ፣የተሰበሰበውን መረጃና የመስክ ምልከታውን በማደራጀት በጋምቤላ ከተማ ለባለድርሻ አካላት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል ብለዋል።

አክለውም በተፋሰስ እቅዱ የዝግጅት ምዕራፍ በየደረጃው ላሉ ባለድርሻ አካላት ለውይይት በማቅረብ አስተያየት እንዲሰጥበት መደረጉን ጠቅሠው የዛሬው ውይይትም በስፋት ምክክር በማድረግ እቅዱ ይሁንታ እንዲያገኝና አቅጣጫ ለማስቀመጥ ወሳኝ ነው ብለዋል።

በእለቱ የውሃ ሀብት፣የመሬት ሀብትና የተፋሰስ ልማት አስተዳደርን በሚመለከት በረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ደረጀ አደባ ፤ ማህበራዊ ኢኮኖሚና ተቋማትን በሚመለከት በረ/ፕ ሞሲሳ ደቻሳና የባለድርሻ አካላት እና ችግሮችን በሚመለከት ደግሞ በረ/ፕ ዮሴፍ ሽፈራው በቀረቡ ዶክመንቶች ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ በክቡር ዶክተር አብርሃ አዱኛ የማጠቃለያ ሀሳብ የእለቱ መርሃ ግብር ተጠናቋል።

Share this Post