የምስራቅ ኢትዮጵያን የሀይል መቆራረጥ ችግር ለመፍታት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ::

የምስራቅ ኢትዮጵያን የሀይል መቆራረጥ ችግር ለመፍታት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ::

በምስራቁ የሀገራችን ክፍል ከፍተኛ የሆነ የሀይል እጥረትና መቆራረጥ ችግርን ለመፍታት ታላሚ ያደረገ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ ክቡር ደ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ገልጸዋል ፡፡

እንደሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ በምስራቁ የሀገራችን ክፍል የሚገኘው የሀይል ማሰራጫ ከ40 አመት በላይ ያገለገለ በመሆኑና አሁን ላይ እያደገ የመጣው የህዝብ ቁጥር ና እየተስፋፋ ካለው የኢኮኖሚ እድገት ጋር ተያይዞ እያጋጠመ ያለው የሀይል መቆራረጥ በህብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታ እያስነሳ መሆኑን ገልጸው ይህን ችግር ለመፍታት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከአሁን በፊት ከነበሩት ማሰራጫ ጣቢያዎች በተጨማሪ 4 ጣቢያዎችን ለመገንባት ወደ ስራ ለመግባት የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም መሰረት በሀረር ከተማ 230 ኬቪኤ ሰብ ስቴሽን ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩንና በተመሳሳይ በሶማሊያ ክልል ፋፈን አካባቢ ጉርሱም ወረዳ የኢንዱስትሪ ዞን ከመሆኑ አንጻር የግብርና ምርቶች፤የመስኖ ፕሮጀክቶች ፤የተለያዩ ፋብሪካዎች እየተገነቡ ስላሉ ኢንቨስተሮች እየገቡበት ያለ በመሆኑ የሚገጥመውን የሀይል እጥረት ለመፍታት 132 ኬቪኤ ለመገንባት ታቅዶ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው አሁን አገልግሎት እየሰጠ ካለው ስቴሽን ጎን ለጎን አገልግሎቱ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡

ክቡር ሚኒስትር ዲኤታው በማያያዝ አሁን እየተገነቡና ሊገነቡ በእቅድ የተያዙ የማሰራጫ ጣቢያዎች ለቀጣይ 20 አመታት ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አንጻር የራሱ የሆነ ድርሻ እንዳለውም ጠቅሰው ይህን ስራ ለመስራት ሲታቀድ የአካባቢውን ማህበራዊ ጫና በመቀነስ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማምጣት ታሳቢ ያደረገ ነውም ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ውጭ ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን በአማራጭ ሀይል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ሲሆን በሀረሪ ክልል ሁለት ትምህርት ቤቶች ላይ እየተገነባ ያለው የሶላር ሚኒ ግሪድ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑንና በተመሳሳይ በደቡብ ኦሮሚያ የተለያዩ የሶላር ሚኒ ግሪዶች በመገንባት ላይ ሲሆኑ የ25 አመት የአገልግሎት ዘመን እንዳላቸውም አክለው ገልጸዋል፡፡

Share this Post