ሶስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ የውሃ አጀንዳ አቅጣጫን ያስቀይራል

ሶስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ የውሃ አጀንዳ አቅጣጫን ያስቀይራል *************** የዓባይ ግድብ ሶስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ ግድቡ እንዳይሠራ ሲጥሩ የነበሩ የውጭ ጠላቶችን የውሃ አጀንዳ አቅጣጫ የሚያስቀይር መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ። የዓባይ ግድብ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ 22 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ይዞ በሁለት ተርባይኖች 750 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ጀምሯል። የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፣ የዓባይ ግድብ የሶስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ የኢትዮጵያን የመደራደር አቅም ከፍ ከማድረጉም በላይ ግድቡ እንዳይሠራ ሲጥሩ የነበሩ ኃይሎችን የ ”ውሃ መያዝ” አጀንዳ የሚያስቀይር ነው። ከግድቡ ሶስተኛ ዙር ሙሌት በኋላ ግድቡን የሚቃወሙ ኃይሎች የሚያነሱት አጀንዳ ውሃ ስለመያዝና ስላለመያዝ አይሆንም ያሉት ሚኒስትሩ፣ የውሃ መያዝ ጥያቄው ቢነሳ እንኳን ለኢትዮጵያውያን የሚሠራ ጥያቄ አይሆንም ብለዋል። እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ፣ በግድቡ ዙሪያ እንደራደራለን የሚሉ ኃይሎች የሚያራግቡት የውሃ መጠን መቀነስን የመሳሰሉና የተለያዩ እውነትነት የሌላቸው ትርክቶች በግድቡ ሶስተኛ ዙር ሙሌት ሃሰትነቱ ተረጋግጧል። በመሆኑም ይህ በራሱ የውሃ መያዝ አለመያዝ አጀንዳቸውን ሊያስቀር የሚችል ነው።

የግድቡ ሙሌት ግንባታው እንዳይከናወን ከሚከላከሉ ኃይሎች አጀንዳ ማሳጣት በተጨማሪ የኢትዮጵያን የመደራደር አቅም ያሳድጋል ብለዋል ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ።

የዓባይ ግድብ ኢትዮጵያ የተናገረችውን መፈፀም የምትችል ሀገር መሆኗን ያሳየችበት ታላቅ ፕሮጀክት ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ የግድቡ ሶስተኛ ዙር ሙሌት መጠናቀቅ የኢትዮጵያን የመደራደር አቅም አሳድጓል የሚባለው በብዙ ምክንያቶች መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት የኃይል ሽያጭ ማቅረብ መቻሏ አንዱ የመደራደር አቅሟን ከፍ የሚያደርገው መሆኑን ጠቁመዋል።

ሌላው የመደራደር አቅምን የሚጨምረው ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል በለማ ቁጥር ብዙ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ መሳብ መቻል መሆኑን አንስተው፤ ከተለያዩ ሀገራት ብዙ ባለሀብቶች ወደ ሀገሪቱ የሚመጡ በመሆኑ ይህ በኢኮኖሚ ትርጉም ያለው ለውጥ ከመፍጠሩም ባሻገር የሀገሪቱን ተሰሚነት ይጨምራል ሲሉም ተናግረዋል።

በተለይ ግድቡ አረንጓዴ የኢነርጂ ምንጭ መሆኑ በጎረቤትና በቀጠናው የተፈጠረውን የመደራደር አቅም መጨመር እና ተፅዕኖ ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነት ከፍ የሚያደርግ መሆኑን አክለው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን ግድቡ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ከፍተኛ ርብርብ ማድረጋቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በግድቡ ዙሪያ ያለፈው ታሪካችን ሲታይ የዓባይ ግድብ እዚህ ደረጃ ይደርሳል ብሎ ማሰብ እንደ ቅዠት የሚቆጠር ነበር ሲሉ አብራርተዋል።

Share this Post