ክቡር ሚኒስትሩ ከአፍሪካ የልማት ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት ጋር ተወያዩ፡፡

ክቡር ሚኒስትሩ ከአፍሪካ የልማት ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት ጋር ተወያዩ፡፡

የካቲት 09/2016 ዓ.ም.(ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የአፍሪካ ልማት ባንክ የሀይል፣ የአየር ጸባይና አረንጓዴ ልማት ዘርፍ ም/ፕሬዝዳንት ሚ/ር ኬቨን ካሩኪ ጋር በታዳሽ ሀይል ልማት እና ተያያዥ የልማት አጀንዳዎች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡

ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በኢትዮጵያ የሀይል ልማት ዘርፉ ሙሉ በሙሉ ታዳሽ ሀይል ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራና የአየር ጸባይ ለውጥን ለመከላከል ብሔራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር አይነተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸው፤ ፖሊሲዎቻንም ሆኑ አተገባበራቸው፤ ከባንኩ ፖሊሲዎች ጋር አብረው የሚሄዱና ናቸው ብለዋል፡፡ ለዚህም የታዳሽ ሀይል ልማት እና የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ጥሩ ማሳያ መሆን እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

ክቡር ሚኒስትሩ አክልውም የንጹህ ማብሰያ ቴክኖሎጂ ማስፋፋት ላይም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጉዳዩን የሚከታተልና የሚተገብር አደረጃጀት ከመፍጠር ጀምሮ በትኩረት እየተሰራበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ በበኩላቸው በአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር የሚተገበሩ የኢነርጂ ልማት ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ የሚታዩ ውስንነቶችን በጋራ እያስተካከሉ መሄድ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢ/ር አሸብር ባልቻ በበኩላቸው ተቋሙ ከልዩ ልዩ የታዳሽ ሀይል ምንጮች የሀይል ማመንጨት ስራዎች ላይ ትኩረት መደረጉን አነስተው፤ ባንኩ የጅኦተርማል ፕሮጀክቶችን እንዲደግፍ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የባንኩ ም/ፕሬዝደንት ሚ/ር ኬቨን ካሩኪ በበኩላቸው ባንኩ ከተቋቋመበት ዋነኛ አላማ መካከል የአፍሪካ ሀገራት የኢነርጂ ልማት ላይ ድጋፍ በማድረግ ዘላቂ ልማት እንዲያረጋግጡ ለማስቻል መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በታዳሽ ሀይል ልማት እና የአየር ጸባይ ለውጥን ለመካላከል የምታደርገውን ጥረት እንደሚያግዙ ተናግረዋል፡፡ ም/ፕሬዝዳንቱ አክልውም ባንኩ ከሚደግፋቸው የኢነርጂ ፕሮከጅኮቶች መካከል አዴል/ADELE (Access to Distributed Electricity and Lighting in Ethiopia) እና ደሪም/DREAM (Distributed Renewable Energy – Agriculture Modalities) ፕሮጀክቶችን አንስተው፤ ከኢትዮጵያ አጋር የሚተገበሩ ፕሮጀክቶችን ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

ም/ል ፕሬዝዳንቱ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዲጂታል ኤግዚቢሽንን ጎብኝተዋል፡፡

Share this Post