በኢትዮጵያ የሶላር ኢነርጂ ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት

ኢንተርናሽናል ሶላር አልያንስ( ISA) በኢትዮጵያ የሶላር ኢነርጂ ቴክኖሎጂን ለማስፋፋትና ጥቅም ላይ ለማዋል በሰነቃቸው ተልዕኮዎች ዙርያ የሚመክር መድረክ እየተካሄደ ነው
 

ኢንተርናሽናል ሶላር አልያንስ ( ISA) በኢትዮጵያ የሶላር ኢነርጂ ቴክኖሎጂን ለማስፋፋትና ጥቅም ላይ ለማዋል በሰነቃቸው ተልዕኮዎች ዙርያ የሚመክር ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡ እ.አ.አ መጋቢት 13/2022 የተጀመረው የምክክር መድረክ እስከ መጋቢት 18/2022 ድረስ እንደሚቆይ ታውቋል፡፡ በምክክር መድረኩ ላይ የኢነተርናሽናል ሶላር አልያንስ ከፍተኛ አመራሮች፣የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርን ጨምሮ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ድርጅቶች፣ የልማት አጋሮችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እየተሳተፉ ነው፡፡

የምክክር መድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ሱልጣን ወሊ ኢትዮጵያ የኢነርጂ ዘርፉን ደረጃ ለማሳደግና ከፍ ለማድረግ እንደ ሌሎች በማደግ ላይ እንዳሉ ሀገሮች ትልቅ ተግዳሮት ያለባት መሆኑን ጠቁመው በ2030 ሁሉንም ዜጎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ የብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ቀርጻ እየተገበረች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ የኢንተርናሽናል ሶላር አልያንስ አባል በመሆኗ በጥምረቱ በሚሠሩ ፕሮግራሞች ዙርያ ፍላጎቷን እንደገለጸች ገልጸው የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል ረገድ ጥምረቱና ሌሎች የልማት አጋሮች ለሚያደርጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ኢንተርናሽናል ሶላር አልያንስ የሶላር ኢነርጂ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ በመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በመስኖ ለሚካሄድ ግብርና፣ በሐይቆች ወይም በግድቦች የውሃ አካላት ላይ ሊንሳፈፉ ፣ በሕንጻዎች ጣርያ ላይ ሊቀመጡ የሚችሉ የሶላር ፓኔሎችን በማድረግ ኢነርጂ ለማመንጨትና ጥቅም ላይ ለማዋል ፤በዚህም ዘላቂ የልማት ግቦች ግብ 7 እና 13 እውን ለማድረግ ሰፊ የፀሐይ ብርሃን ሀብት ባላቸው 102 ሀገራት ውስጥ የሚሠራ የሀገራት ጥምረት ነው፡፡

ጥምረቱ ለአባል ሀገራቱ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ፣ የቴክኒክ ድጋፎችን በማድረግ፣ ማሳያ ፕሮጀክቶችንም ከየሀገራቱ መንግሥታት ወይም ተቋማት ጋር በጥምረት በመገንባት የሶላር ኢነርጂ ቴክኖሎጂ በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውል የሚሠራ ድርጅት ነው፡፡

Share this Post