በውሀ ሀብት አጠቃቀም ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ቅንጅታዊ አሰራር መከተል እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

በውሀ ሀብት አጠቃቀም ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ቅንጅታዊ አሰራር መከተል እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

ጥር 20/2016ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ በብሄራዊ የተቀናጀ ውሀ ሀብት አስተዳደር ፕሮግራም ዙሪያ ከክልል እና የቤዚን አስተዳደር ጽ/ቤት ባለሙያዎች ጋር ውይይት አደረገ፡፡

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሀ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ዶ/ር አብርሃ አዱኛ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አደረጃጀቱን አሻሽሎ ወደ ተግባር ሲገባ የተቀናጀ የውሀ ሀብት አስተዳደር ማስፈን ከሚጠበቅበት ውጤት አንደኛው መሆኑን ጠቅሰው፤ የውሃ ሀብትን በተቀናጀ መልኩ ለማልማት የውሀ መጠን የመለየት፤ ጥራቱን የመጠበቅ፤ የግኝት ሁኔታን በቦታ የመለየት፤ አጠቃቀሙን የመወሰንና የውሃ ሀብቱን የመጠበቅና የመንከባከብ ጉዳዮችን ለማከናወን የውሃ ሀብቱን የማስተዳደር ሂደት በተለየ ሁኔታ ቅንጅታዊ አሰራር ማስፈን እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በማያያዝ ውሀን መሰረት አድርገው ወደ ልማት የሚገቡ አካላት በሙሉ አቀናጅቶ በአንድ ላይ፤ በአንድ እቅድ መሰረት አድርገው ወደ ልማት የሚቀይሩበት የውሃ ሀብት አስተዳደር ረቂቅ ፖሊሲ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡

የውሃ ሀብት አስተዳደርን ለማስፈን የሚያግዙ የተለያዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ የህግ ማእቀፎችም ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸው፤ በየውሀ ሀብት አስተዳደርን ለማስፈን እንደ ሀገር ትኩረት ተሰጥቶት መስራት እንደሚገባ በማንሳት መርሀ ግብሩን አስጀምረዋል፡፡

መርሀ ግብርሩ ላይ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው “የውሃ ሀብት አስተዳደር በኢትዮጵያ” በሚል ርእስ የተዘጋጀ ሰነድ አቅርበዋል፡፡ በሰነዱ የተቀናጀ ውሀ ሀብት የነበረበትን እና አሁን ያለበት ደረጃ በደረጃ ገለጻ ያድረጉ ሲሆን በተለይ በኢትዮጵያ ውሀን መጠቀም፤ ማልማት፤ መጠበቅና መቆጣጠር በሚቻልበት እና በሌሎች የውሀ ሀብት አስተዳደደር ነክ ጉዳዮች ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡

መርሀ ግብሩ ለሁለት ቀን የሚቆይ ሲሆን፤ ውሃ ሀብትን በተመለከተ የተለያዩ ሰነዶች ለውይይት እንደሚቀርቡ ከአስተባባሪዎቹ መረዳት ችለናል፡፡

Share this Post