''የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር መልሶ ይከፍለናል'' ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ

''የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር መልሶ ይከፍለናል'' ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ውኃና ኢነርጂ ሚንስትር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በደቡብ ኮሪያ - ሲዎል ለአራተኛ ጊዜ እየተካሄደ በሚገኘው የ2022 የከባቢ፣ ማኅበራዊና አስተዳደር (2022 Environment, Social and Governance – ESG Forum ላይ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታና እየተወሰዱ ያሉ የመፍትሔ አማራጮችን ለጉባኤው አቅርበዋል፡፡ በጉባኤው ላይ የከርሰ ምድር ውኃን አቅም ለመጠበቅና ከተቻለም ለመጨመር ምን መደረግ አለበት በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ ተፈጥሮን ለመጠበቅ የምናደርገው ጥረት ወሳኝነት አለው፤ ለዚህም ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት በክቡር የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐብይ አሕመድ መሪነት ሲደረግ የነበረውን የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም እንደ አብነት በማንሳት ይህ ተግባራችን መልሶ ይከፍለናል በማለት ገልጸዋል፡፡ ክቡር ሚንስትሩ የደቡብ ኮሪያን የውኃ ኮርፖሬሽን ተቋማትም ጎብኝተዋል፤ በጉብኝቱ በርካታ የትብብር ዕድሎች እንዳሉ ያነሱት ሚንስትሩ ነሐሴ 24/2014 ዓ/ም በተፈራረሙት የትብብር ስምምነት መሰረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር ሊለወጡ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ አንስተው ከኮርፖሬሽኑ በጎ ምላሽ አግኝተዋል፡፡ በሌላ በኩል ክቡር ሚንስትሩ በትናንትናው ዕለት ከጉባኤው ጎን ለጎን በደቡብ ኮሪያ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር ሥር ከሚገኘው የሀገሪቱ የከባቢ ኢንደስትሪ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲቱት (Korea Environmental Industry and Technology Institute – KEITI) ምክትል ፕረዚደንት ሊ ዊዎንና የሥራ ኃላፊዎች ጋር በሁለትዮች ትብብር ላይ ተወያይተዋል፤ በውይይቱም በዘርፉ ለሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ሊሰጡ በሚችሉ የትምህርት ዕድሎችና ሌሎች አንኳር ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

Share this Post