አባይን ለመገደብ የተከፈለ ትልቅ ዋጋ!
ወ/ሮ አሰለፈች ጸጋዬ ይባላሉ ነዋሪነታቸው ሻሸመኔ ከተማዋ 05 ቀበሌ ሲሆን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባዘጋጀው አገር አቀፍ አውደ ርዕይ ያገኘናቸው ጀግና እናት ናቸው።
ወይዘሮዋ የተለያዩ የባልትና ውጤቶችን በመሸጥ የሚተዳደሩ ሲሆኑ በ2003 ዓ.ም አባይን ለመገደብ የመሠረት ድንጋይ ሲጣል የተደሰቱበትን ቅጽበት ይናገራሉ ። በዚህ የተደሰቱት ወይዘሮዋ ታዲያ የተረፋቸውን ሳይሆን ያላቸውን 1000 ብር ቦንድ በመግዛት የዘመናት ቁጭታቸውን ለመወጣት ድጋፋቸውን አንድ ብለው መጀመራቸውን በአንደበታቸው ይናገራሉ።
አባይ ሲገደብ፣ ኢትዮጵያ ስትበለጽግ እኔም አብሬ አድጋለሁ የሚል መርህ የታጠቁት እናት ምንም ሳይታክቱ ሳይተርፋቸው ያላቸውን ሳይሰስቱ በመለገስ በስጦታ ያበረከቱት ሳይቆጠር እስካሁን የስድስት መቶ ሺ ብር ቦንድ ገዝተዋል።
ወይዘሮዋ ይህም ብቻ ሳይሆን በአካባቢያቸው በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው እና በማንኛውም ልማት ንቁ ተሳታፊ በመሆናቸው በተለያዩ ጊዜያት ያገኟቸው ሽልማቶች ምስክር ናቸው።
ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከስፍራው ተገኝተው ሁለት ጊዜ እንደጎበኙ የሚናገሩት ወይዘሮዋ ለአባይ ግድብ እንኳን ገንዘቤን ስጋየን ቆርጨ ብሰጥ ቅር አይለኝም ይላሉ፤ በሰጠሁ ቁጥር አምላኬ በበረከት ይጎበኘኛል የሚሉት እናት በየጊዜው የነበሩ መሪዎች የራሳቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል። አሁን ላይ ግድቡ በዚህ ደረጃ ሆኖ ከማየት የበለጠ የሚያስደስት ነገር የለም በማለት በእናትነት አንደበት ይናገራሉ።
በ2016 ቦንድ በመግዛት ያላቸውን የሀገር ፍቅር ለመግለጽ ቆርጠው እንደተነሱ የሚናገሩት እናት የኢትዮጵያ ህዝብ ፍቅር ነው እንኳን ለአባይ ለሌላም ይሰጣል። አሁንም በተጀመረው አግባብ ግድባችን እንዲጠናቀቅ ሁላችንም እንደግፍ ። ብር ዝም ብለው ቢያስቀምጡት ትርጉም የለውም በማለት የእናትነት ምክራቸውን ለግሰዋል።