ጎርፍን ከስጋትነት ባሻገር እንደ እድል መጠቀም እንደሚገባ ተነገረ።
ነሐሴ21/ 2015 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ.) የጎርፍ ውሃ በአግባቡ ከተጠቀምንበት እድል እንጂ ስጋት አለመሆኑን የጎርፍ አደጋ ተገለጭነት እና የቅድመ መከላከል ተግባራት ላይ ገለጻ ካደረጉ ባሙያዎች መረዳት ችለናል።
በኢትዮጵያ የመሬት አቀማመጥ እና በሰው ሰራሽ ምክንያቶች የጎርፍ አደጋዎች በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሠረተ ልማቶች ላይ ተፅዕኖ ሲያሳደር መቆየቱን የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ስር የተፋሰስ ልማት እና የቅድመ ጎርፍ መከላከል ዴስክ ሃላፊ አቶ ደጀኔ ለገሰ አስረድተዋል። ይህንን ችግሮች ለመፍታት የጎርፍ ተጋላጭ አከባቢዎች በመለየት የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ በማዘጋጀት መከላከል እንደሚቻል ገልጸው፤ የመሬት ከፍታ (በደጋ እና ወይናደጋ ) አካባቢዎች የተጀመረው የችግኝ ተከላ በማጠናከር የክረምት ዝናብ ወደ መሬት ሰርጎ እንዲገባ በማድረግ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በሌላ በኩል በቆላማና ዝናብ አጠር አከባቢዎች የጎርፍ ክስተቶች በመሠረተ ልማቶች ላይ ውድመት እንዳያስከትል የወንዝ አመራር ስራና ግድቦችን በመገንባት ዘላቂ የጎርፍ ቅድመ መከላከል ሥራዎች መስራት እንደሚቻል ገልፀዋል ።
በሌላ በኩል የጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት አስተባባሪው አቶ ተመስገን ከተማ በበኩላቸው ከዚህ በፊት በተለየ ጊዜ ለኃይል ማመንጫና ለመስኖ ሥራዎች የተሠሩ ግድቦች የክረምት ዝናብ በማሰባሰብ ለጎርፍ መከላከል ሥራ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ጠቅሰው በቀጣይ ቅድመ ጎርፍ መከላከልን አላማ ያደረገ ሥራ በዘላቂነት ለማከናወን ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ በኦሞ ጊቤ፣ በስምጥ ሸለቆ እና በአዋሽ ቤዚኖች የትግበራ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል ። በተጨማሪም በ4 ቤዚኖች ላይ የኢንቨስትመንት እቅድ ጥናት ለማካሄድ መታቀዱን አብራርተው የቅድመ ጎርፍ መከላከል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ መኖሩን የገለፁት አስተባባሪው በግድቦቹ በሚጠራቀሙ የጎርፍ ውሃ ለመስኖና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት በማዋል ድርቅን መቋቋም የሚችል ኢኮኖሚ መፍጠር ያስችላል ብለዋል።