ስትራቴጂክ ቤዚን ፕላን የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስርዓትን እውን ማድረጊያ ቁልፍ መሳሪያ መሆኑ ተገለፀ።
ሰኔ/2015 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአዋሽ ቤዚን አስተዳደር ፅ/ቤት ''አንድ ቤዚን አንድ እቅድ'' በሚል ሃሳብ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ከግንቦት 29/2015---ሰኔ 03/2015 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው ውይይት ተጠናቀቀ።
በማጠቃለያ መርሀግብሩ ላይ የተገኙት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ በላይነህ ይርዳው ሚኒስቴር መ/ቤቱ የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፉን ማጠናከር ላይ በትኩረት እንደሚሰራ፣ እቅዱን ወቅታዊና ተጨባጭ ከማድረግ አንፃር የሀብት፣ የጊዜና የበጀት ብክነት እንዳይኖርና ድግግሞሽ እንዳይፈጠር እንዲሁም ቀጣይነቱን የማረጋገጥ ስራ ላይ ሁሉም የሚመለከተው አካል እቅዱን መረዳት፣ ማስረዳትና ለተግባራዊነቱ የድርሻችንን እንወጣ በማለት አሳስበዋል።
በሚ/ር መስሪያ ቤቱ የሀይድሮሎጂና የተፋሰስ መረጃ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ የተፋሰስ ዕቅድ ትግበራ ስትራቴጂ በሚ/ር መስሪያ ቤቱ እየተዘጋጀ እንደሆነ ገልፀው ከባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ጋር ያለውን ግንኙነት እንደሚያጠናክርና በዚህ መድረክ ያልተሳተፉ ተቋማትን ተግባርና ኃላፊነታቸው ላይ በማወያየት ትስስር ለመፍጠር በሚ/ር መስሪያ ቤቱም ሆነ በአዋሸ ቤዚን አስተዳደር ፅ/ቤት በትኩረት ሊታይ እንደሚገባ ገልፀዋል።
የአዋሸ ቤዚን አስተዳደር ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አንድነት ጌታቸው በበኩላቸው የተፋሰስ እቅድ በ2009 ዓ.ም እንደተጀመረ ገልፀው በአዋሽ ተፋሰስ ቴክኒካል ኮሚቴዎችና ባለሙያዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ተሰርቶ ለተፋሰስ ም/ቤት የቀረበበትን አግባብ አስታውሰው የተፋሰስ ልማትና እንክብካቤ ተግባር የሁሉም ሴክተር ጉዳይ በመሆኑ ተቋማት በየጊዜው በተደራጁ ቁጥር አዳዲስ አመራሮችና ባለሙያዎች በመሆናቸው ለእቅዱ አዲስ ሲሆኑ ትግበራው ላይ ክፍተት እንደፈጠረባቸው ገልፀዋል፡፡
ውይይቱ በአራት የትኩረት መስኮች (Thematic Area) ዙሪያ /በውሃ ጥራት፣ በውሃ ምደባ፣ በተፋሰስ ልማትና እንክብካ እና በጎርፍና ድርቅ አስተዳደር/ ሲሆኑ ተፋሰሱን ከሚጋሩ ክልሎች ከአፋር፣ ከኦሮሚያ፣ ከአማራ ክልል፣ ከአዲስ አበባ መስተዳድርና ከሚመለከታቸው የፌዴራል ተቋማት ተሳትፈው እቅዱን ከሴክተራቸው እቅድ ጋር በማቀናጀትና በማስተሳሰር ሂደት ላይ ውይይት ተደርጎበታል፡፡