ኢትዮጵያ የሶላር ኢነርጂ እቃዎችን መገጣጠምና ማምረት በምትችልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተደረገ፡፡

ኢትዮጵያ የሶላር ኢነርጂ እቃዎችን መገጣጠምና ማምረት በምትችልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተደረገ፡፡ ግንቦት 29/2015ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከሶላር ማምረቻና መገጣጠሚያ ግብረሃይል ጋር በዘርፉ ያሉትን ተግዳሮቶች በመፈተሸ ሊወሰዱ በሚገባቸው የመፍትሄ ሀሳቦች ዙሪያ በካፒታል ሆቴል ውይይት ተደረገ፡፡ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የገጠር ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር ስራ አስፈጻሚ አቶ ብርሃኑ ወልዱ ባደረጉት ንግግር ባለፉት ዓመታት ከዜጎች የሀይል ፍላጎት አኳያ ከቤተሰብ ሶላርና ከሶላር ሚኒ ግሪድ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራበት ያለ እና በዘርፉ ያለው ኢንቨስትመንትም እያደገ የመጣ ቢሆንም በሀገር ደረጃ ከተቀመጠው ግብ አኳያ አመርቂ አለመሆኑን ገልጸው በሚፈለገው ልክ ለመስራት የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የቴክኖሎጂዎች ዋጋ ንረት፣ የጥራት ጉድለቶች፣ የብድር አገልሎት ተደራሽ ያለመሆንና የቴክኖሎጂ ሽግግር አናሳ መሆን ማነቆዎች ናቸው ብለዋል፡፡ አክለውም የኦፍ ግሪድ ቴክኖሎጅዎችን በአገር ውስጥ ማምረት የገጠሩን ማህበረሰብ የቴክኖሎጅ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የጥራት ደረጃን ለማስጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ችግሮችን በመለየት የመፍትሄ ሃሳብ የሚያቀርብ ከተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት እንዲሁም ከሲቪል ማህበራት የተውጣጡ ግብረሃይል ሲመራ መቆየቱን እና ከነዚህም መካከል አንዱ የኦፍግሪድ ሶላር ማኑፋክቸሪግ ዘርፍ አንዱ በመሆኑ መድረኩ በሃገራችን በኦፍግሪድ ማኑፋክቸሪግ ዘርፍ ያሉትን ተግዳሮቶች በመፈተሸ እንዲሁም ሊወሰዱ የሚገባቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች በማቅረብ በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ ለውይይት መነሻ የሚሆን የፕሪሳይስ የኦፍግሪድ ማናጀር በሆኑት በአቶ አቤል እንድሪያስ ኢትዮጵያ ውስጥ ሶላር ማምረትና መገጣጠም በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ያሉ ግኝቶችን የሚያስረዳ ሰነድ የቀረበ ሲሆን በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ እና መብራት ስርጭትን ተደራሽ የማድረግ ፕሮግራም ADELE (Access to distributed electricity and lighting in Ethiopia) የፋይናንስ አማራጮች ምን እንደሆኑ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የ ADELE አስተባባሪ በሆኑት በአቶ አዲስአለም መብራቱ ቀርቧል፡፡ በእለቱ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር በዘርፉ ላይ ያላቸው ተሳትፎ ምን እንደሚመስል በተወካዮቻቸው አማካኝነት ያቀረቡ ሲሆን ሶላር በማምረትና በመገጣጠም ስራ ላይ የተሰማሩት የፎዜራ ማኑፋክቸሪግ ፒኤልሲና አብራምባ ቴክኖሎጅስ ያሉባቸውን ችግሮችና በቀጣይ ከችግሩ እንዴት መውጣት አለባቸው በሚሉ ጉዳዮች ላይ በርካታ ሃሳብ አስተያየቶች እንዲሁም የመፍትሔ ሃሶች ተንጸባርቀዋል፡፡

Share this Post