የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ተቋማት የግንባታ ሂደት ቁጥጥርና ክትትል ማንዋሎች ዝግጅት

  የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ተቋማት የግንባታ ሂደት ቁጥጥርና ክትትል ማንዋሎች /Guidelines ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ተገለጸ፡፡ ከማንዋሎቹ አተገባበር ጋር በተያያዘ ከከልሎችና ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለተውጣጡ ባለሙያዎች ስልጠናና ማንዋሎቹ ሁሉንም የሀገሪቱን አካባቢዎች ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘቡ እንዲሆኑ የሚያስችል ማበልፀጊያ ወርክ ሾፕ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል፡፡ በስልጠናውም ለተሳተፉ ባለሙያዎች ሰርተ ፍኬት ተሰጥተዋል፡፡ ስልጠናውና ወርክሾፑ በተጠናቀቀበት ጊዜ በስፍራው የተገኙት የመጠጥ ውሃሳ ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ተቋማት የግንባታ ሂደት ቁጥጥር እንደሚፈልግ ገልጸው ቁጥጥር የማይደረግበት ግንባታ ብዙ ኪሣራ ያደርሳል ብለዋል፤ በዚህም ምክንትን በውሃ ተቋማት የግንባታ ሂደት በምን በምን ጉዳይ ላይ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ እንደሚገባ ስልጠና መሰጠቱ፣ የሚገነቡት ተቋማት ረጅም ጊዜ የሚያገለግሉ ፣የፈሰሰባቸውንም ገንዘብ ዋጋ የሚመልሱ እንዲሆኑ በማሰብ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የግንባታ ቁጥጥርና ክትትል ማንዋሎች ለዘርፉ አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቁመው ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በማበልፀጊያ ወርክ ሾፑም ለተሳተፉና ገንቢ አስተያዬት ላበረከቱ የክክልና የፌደራል ባለሙያዎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በየክልሎቹም ባገኙት እውቀት ለሀገራቸውን ለኅብረተሰቡ ጠቃሚ ሥራ እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡ የግንባታ ሂደት ቁጥጥርና ክትትል ማንዋሎቹ የሚገነበሩ የውሃ ተቋማት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገሩ እንዲሆኑ ከማስቻሉም በላይ ከውሃ ተቋማት ከውሃ ምንጭ መረጣ ጀምሮ ፣የውሃ ጉድጓድ ቁፎሮ፣ የኤሌክትሮ መካኒካል ግንባታን አካቶ ውሃው ተጠቃሚዎች ዘንድ እስኪደርስ ድረስ የሚኖረውን የግንባታ ሂደት ለመቆጣጠርና ለመከታተል የሚያስችል መሆኑ በመድረኩ ላይ ተነስቷል፡፡ የመጠጥ ውሃ ተቋማት የግንባታ ሂደትም በተያዘላቸው በጀትና በተቀመጠላቸው ጊዜ ገንብቶ ለማጠናቀቅ ፣ የታቀደላቸውንም ያህል ዓመታት ያለ እንከን ኅብረተሰቡን ውሃ ማቅረብ የሚችሉ ተቋማትን ለመገንባት እንደሚያስችል ተጠቁሟል፡፡ በስልጠናና ወርክ ሾፑ ላይ ከክልልና ፌደራል መንግሥት ተተውጣጡ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

Share this Post