የዜጋ ክብር እና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ አዲስ ምዕራፍ:- መጋቢት 24
መጋቢት 24/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የለውጡ መንግስት ሀገራዊ ኃላፊነትን ሲረከብ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን በመከተል የዜጋ ክብር የጀመረበት አዲስ ምዕራፍ ነበር፡፡
ለውጡ ሲጀምር መንግስት የዜጎችን ደህንነትና መብት ማስከበርን ቀዳሚ የዲፕሎማሲ አጀንዳ አድርጎ ያሳየው ቁርጠኝነት ከቃላት ባለፈ በተግባር የተፈተነ፤ በተለይም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ወደ ተለያዩ አገራት ባደረጓቸው ጉብኝቶች ሁሉ በእስር ላይ የሚገኙ ወገኖችን በገዛ አውሮፕላናቸው ጭምር ይዘው በመመለስ ያሳዩት አርአያነት፣ መንግስት ለዜጎቹ የሚሰጠው ዋጋ ምን ያህል ከፍ ያለ መሆኑን ለመላው ዓለም ምሳሌ ሆኗል፡፡
በሌሎች አገራት የሚገኙ ዜጎች መብታቸው እንዲከበር ከሀገራቱ ጋር የተደረጉ የሁለትዮሽ ስምምነቶች፣ ዜጎች በሰው አገር የበይ ተመልካች ሳይሆኑ በህግ የተጠበቀ ክብር እንዲኖራቸው አስችሏል፤ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖችን ወደ አገራቸው በመመለስ ረገድ የተከናወነው የተቀናጀ ስራ፣ የመንግስትን የመፈፀም አቅምን በተግባር አሳይቷል፡፡
የለውጡ መንግስት ዲያስፖራውን እንደ ባዕድ ወይም እንደ ስጋት የመመልከት ጠባብ አስተሳሰብ በመስበር፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በዓለም አቀፍ መድረክ የአገሩን ክብር ተካፋይ እንዲሆን አድርጓል፡፡
ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲው ኢትዮጵያን ለዜጎቿ የምትቆም አገር መሆኗን ከማረጋገጡም በላይ፣ የውጭ ግንኙነታችንን ከደረቅ ቢሮክራሲ ወደ ህያውና ሰው ተኮር ግንኙነት በመቀየር አገራዊ ኩራታችንን ከፍ አድርጎታል፡፡
በአጠቃላይ መጋቢት 24 ኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተችበትና ሀገራዊ ኃላፊነትን የተረከበችበት ታሪካዊ ዕለት ነው፡፡ ባለፉት ዓመታትም ከተመዘገቡ ስኬቶች መካከል በአንድ ዘርፍ ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ የነበረው የኢኮኖሚ መዋቅር ወደ ብዝሃ ዘርፍ እንዲሸጋገር የተደረገው ጥረትና ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ያመጣቸው ውጤቶች ይጠቀሳሉ፡፡
በተመሳሳይ በቱሪዝም ዘርፉ ገበታ ለሀገር፣ ገበታ ለሸገርና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች አማካኝነት አዳዲስ መዳረሻዎች መፈጠራቸው ለሀገር ገፅታ ግንባታ ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡