በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ እየተሰራ ነው - ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ እየተሰራ ነው - ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20 ቀን 2018 (ው.ኢ.ሚ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ እየተሰራ መሆኑን በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ገለጹ።
በክልሉ ቡታጅራ እና ሆሳዕና ከተሞች የሚካሄዱ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ግንባታ ፕሮጀክቶች በፍጥነት ለአገልግሎት እንዲበቁ ለመደገፍ የሚያስችል ምልከታ ተካሂዷል።
ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ሀይሉን ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በጉብኝቱ ተገኝተዋል።
ጉብኝቱ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ ተቋማት ለማነቆዎች መፍትሔ ለመስጠት እንደሚያስችላቸው ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ተናግረዋል።
በሆሳዕና ከተማ የሚካሄደው የፍሳሽ ማጣሪያ ፕሮጀክት በጥሩ አፈፃፀም ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ፕሮጀክቱ ለአገልግሎት እንዲበቃ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
በተለያዩ ከተሞች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የሆሳዕና ከተማ የፍሳሽ ማጣሪያ/የሳኒቴሽን ፕሮጀክት አፈፃፀም ግንባታ በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የጠቀሱት ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ፤ ፕሮጀክቱ ተጠናቅቆ ወደ ተግባር ሲገባ ለህብረተሰቡ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚሰጥም አመላክተዋል።
በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው የዚህ ፕሮጀክት የግንባታ ፍጥነት ለሌሎች አካባቢዎች ተሞክሮ እንደሚሆን አስረድተዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ሀይሉ በበኩላቸው፤ የቡታጅራና የሆሳዕና ከተሞች ሳንቴሽን ፕሮጀክቶች በሀገር ደረጃ ሊጠቀሱ የሚችሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ናቸው ብለዋል።
በክልሉ በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኘው የሆሳዕና ከተማ ፍሳሽ ማጣሪያ ፕሮጀክት ባጠረ ጊዜ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃም ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ በጥሩ አፈጻጸምና በተሻለ ቁመና ላይ እንደሚገኝ የጠቆሙት ኃላፊው፤ ባለድርሻዎች በቁርጠኝነት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።