በግንባታ ላይ የሚገኙ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የቅርብ ክትትል እየተደረገ ነው - ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ

በግንባታ ላይ የሚገኙ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የቅርብ ክትትል እየተደረገ ነው - ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19 ቀን 2018 (ው.ኢ.ሚ) በግንባታ ላይ የሚገኙ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ገለጹ።

ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ፣ የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ሀይሉ ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ በዓለም ባንክ ድጋፍ እየተገነባ የሚገኘውን የንፁህ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክትን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ እንደገለጹት፤ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ ነው።

በወራቤ ከተማ ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ወጪ እየተገነባ ያለው የዓለም ባንክ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክትን በአብነት ጠቅሰዋል።

ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልን ጨምሮ በሀገሪቱ የተጀመሩ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የድጋፍና ክትትል ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን አንስተው፤ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ተገቢውን ድጋፍና ክትትል እያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።

ፕሮጀክቶቹን በአጭር ጊዜ አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጀምሮ በየደረጃው ተከታታይ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በክልሉ በተለያዩ ከተሞች እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ ስራ ሲገቡ የከተሞችን ጽዳትና ውበት ከማጎልበት ባለፈ የከተሞችን ገጽታ በመቀየር ረገድ ትልቅ ሚና እንዳላቸው የክልሉ ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ኢነርጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ሀይሉ አንስተዋል፡፡

የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ በበኩላቸው፤ በወራቤ ከተማ እየተገነባ ያለውና የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ የሚገኘው የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ለአገልግሎት ሲበቃ የህብረተሰቡን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚነት ያረጋግጣል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ዋና ዋና የሲቪልና የኤሌክትሮመካኒካል ስራዎችን አጠናቅቆ በማጠቃለያ ምዕራፍ ላይ መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፤ 2 ሺህ ኪዩቢክ ሜትር የውሃ ማጠራቀሚያ፣ 4 ጥልቅ ጉድጓዶች እንዲሁም የመብራት ትራንስፎርመሮችን ያካተተ ነው።

በተመሳሳይ በ540 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተገነባ የሚገኘው የቡታጀራ ከተማ የፍሳሽ ማጣሪያ ፕሮጀክቶችን የስራ እንቅስቃሴ የተጎበኘ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ የከተማ ውበት፣ ጽዳትና ገጽታ በመቀየር ረገድ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል።

Share this Post