በኦሞ-ጊቤ ተፋሰስ ዕቅድ ቴክኒካል ቡድን የኦዲት ሪፖርት ክለሳ ዙሪያ የተዘጋጀው የባለድርሻ አካላት መርሃ ግብር በርካታ ግብዓቶች ያገኘንበት በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

በኦሞ-ጊቤ ተፋሰስ ዕቅድ ቴክኒካል ቡድን የኦዲት ሪፖርት ክለሳ ዙሪያ የተዘጋጀው የባለድርሻ አካላት መርሃ ግብር በርካታ ግብዓቶች ያገኘንበት በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ ተሳታፊዎች ገለፁ። ጅማ፣ ግንቦት 9/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በዚሁ ሁነት ላይ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የዘርፉ ስራ አስፈጻሚዎችና ባለሙያዎች፣ ከውሃና መሬት ሃብት ማዕከል የብራይት ፕሮጀክት አስተግባሪዎች፣ ከደቡብ  ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና ከኦሮሚያ ክልሎች የተፋሰሱ አስፈፃሚዎች፣ ከከፍተኛ የምርምር ተቋማት ተመራማሪዎች፣ ከግልና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከዘርፉ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሌሎች ተሳታፊዎች የታደሙበት ሲሆን የተፋሰሱ ቴክኒካል ቡድን ኦዲት ሪፓርትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች እየተቃኙበት ለሁለት ቀናት ተካሂዶ ተጠናቋል። መድረኩ የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ዕቅድ ትግበራን ለማሳካት በስራ ሃላፊነታችን የተሰጠንን ተልዕኮ ለማሳካት በርካታ ግብዓቶች ያገኘንበት በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉም በቃለመጠይቃችን ያነጋገርናቸው ተሳታፊዎች ገልጸዋል። ዶ/ር አስካለ ገ/ሚካኤል በሚዛንቴፒ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዳይሬክተር ሲሆኑ ሃገራችንን ለመለወጥ ያላትን ሃብት በአግባቡ ማስተዳደር ስላለብን በዚህ ዘርፍ ለሚያጠኑ አጥኚዎች ጥቆማ ለመስጠትና በምርምርና ጥናቶች የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመለየት እገዛ የሚያደርጉ መሠረታዊ ነጥቦችን ያስተዋልኩበት ስለነበር መድረኩ አሰፈላጊ ሆኖ አግኝቸዋለሁ ብለዋል። በጂንካ ዩኒቨርስቲ የማህበራዊ አንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል ሃላፊና ተመራማሪ መ/ር አጋፋሪ ሰለሞን በበኩላቸው በተፋሰሱ ቴክኒካል ቡድን ኦዲት ሪፓርት ሂደት የነበራቸው ሚና የማህበራዊ ኢኮኖሚ ትንተና ማካሄድ፣ በተፋሰሱ ከጎርፍ መጥለቅለቅ ጋር በተገናኘ በሚያጋጥሙ ተፈጥሯዊና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ዙሪያ ምርምር ማድረግና የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ባካሄደው ጥናት ላይ ክለሳ በማድረግ ግብዓት ለመስጠት በዚህ መድረክ ላይ መገኘታቸውን አስረድተዋል። በቦንጋ ከተማ ናቡ ኢትዮጵያ ከተባለው መንግስታዊ ካልሆነ ድርጅት የተጋበዙት አቶ አየነው መኮነንም በድርጅቱ የሳይት አስተባባሪ ሲሆኑ ድርጅታቸው የተፈጥሮ ሃብትና የደን እንክብካቤ ልማት እንክብካቤ ጥበቃና ለአካባቢው ማህበረሰብ የኑሮ ማሻሻያ ስራዎችን የመደገፍ ስራ እንደሚሰራ አስረድተው የኦሞ- ጊቤ የተፋሰስ ዕቅድን የሚመለከት ስራም በድርጅታቸው በሚተገበር ፕሮጀክት ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በመድረኩም በዚህ ሂደት የነበሩ ክፍቶችን በመለየት በቀጣይ የሚካተቱ ማሻሻያዎችን መርምረንበታል ብለዋል። አብዛኞቹ ተሳታፊዎችም መርሃ ግብሩን በጋራ ላዘጋጁት ለውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና ለውሃና መሬት ሃብት ማዕከል ምስጋናቸውን አቅርበው በሪፓርቱ የተካተቱ በርካታ ጉዳዮችን መሠረት በማድረግ ለዕቅዱ ክለሳና ለተግባራዊነቱ የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

Share this Post