የተፋሰስ ዕቅድ ትግበራን በማረጋገጥ የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደርን ዕውን ማድረግ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ይጠይቃል-አቶ ደበበ ደፍርሶ
ግንቦት 8/2018 ዓ.ም (ው.ሚ.ኢ) ጅማ የተፋሰስ ዕቅድ ትግበራን በማረጋገጥ የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደርን ዕውን ማድረግ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ይጠይቃል ሲሉ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ አሳሰቡ።
አቶ ደበበ ይህንን ያሳሰቡት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከውሃና መሬት ሃብት ማዕከል ጋር በጋራ የሚተገብሩት የብራይት/BRIGHT/ ፕሮጀክት አካል የሆነው የኦሞ-ጊቤ ተፋሰስ ዕቅድ ቴክኒካል ኦዲት ሪፖርት በቀረበበት የባለድርሻ አካላት የውይይት መርሃ ግብር ላይ ነው።
እንደ አቶ ደበበ ገለጻ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደርን በአግባቡ ለመምራት እንዲያመች ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል የተፋሰስ ዕቅድ ዝግጅት፣ክለሳና የኦዲት ሪፖርት የማረጋገጥ ስራ ተቀዳሚ ተግባሩ እንደሆነ አመልክተዋል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢትዮጵያ በህግ የተደነገጉ 12 ተፋሰሶች ያሏት ሃገር እንደመሆኗ መጠን እነዚህ ተፋሰሶች የውሃ ሃብታቸው የውሃ ፍሰት ወሰንን የተከተለ በመሆኑ ይህንን መሠረት በማድረግ በክልሎችና በሴክተሮች ማዕከል ያሉትን የተለያዩ ስትራቴጂክ ዕቅዶች በማሰባሰብ የዕቅድ አሃድ አድርጎ በመውሰድ ዋናው የተፋሰስ ዕቅድ የሚዘጋጅ መሆኑን አብራርተዋል።
አያይዘውም የተፋሰስ ዕቅድ ተዘጋጅቶ የአስራ አምስት ዓመት የጊዜ ቆይታ እንደሚኖረው አመልክተው ቀደም ሲል በጣና በለስ ፕሮጀክትና፣ በአባይ ተፋሰስ መጀመሩንና፣ አዋሽ ተፋሰስ ላይ ደግሞ በተሻለ መንገድ ተዘጋጅቶ እንደነበረና አስከ አሁን ድረስም በሰባት ተፋሰሶች ላይ ተግባራዊ ማድረግ መቻሉን አስገንዝበዋል።
ከእነዚህ ተፋሰሶች መካከል የአዋሽ ተፋሰስ ዕቅድ ተጠናቆ ክለሳ እየተደረገበት መሆኑንና የአባይና ስምጥ ሸለቆ ተፋሰሶች ዕቅድ ደግሞ ወደ ትግበራ የተገባበት መሆኑን ጠቅሰው በዕለቱ መርሃ ግብር ላይ የቀረበው የኦሞ-ጊቤ ተፋሰስ ዕቅድ ቴክኒካል ኦዲት ሪፓርት ደግሞ በ2024 ተጠናቆ በ2025 (እ.ኤ.አ) ወደ ስራ የተገባበት ዕቅድ መሆኑን አቶ ደበበ አክለው ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት ዕቅዱ አጭር የትግበራ ጊዜ ቢኖረውም በየጊዜዉ መከለስ ዓብይ ተግባር በመሆኑና ቀደም ሲል ባለድርሻ አካላት የነበራቸው ቅንጅትና ተሳትፎ ውስን በመሆኑ በሂደት መፍትሔ ለመስጠት እንዲቻል ኦዲት ለማድረግ መድረክ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኗልም ብለዋል።
በዚሁ መድረክ ቀድሞ የተዘጋጀው የኦሞ -ጊቤ የተፋሰስ ዕቅድ ስምምነቶች፣ ለትግበራ አመቺነቱ ፣አዳዲስ ለውጦችን የማስተናገዱ ጉዳዮች፣ የባለድርሻ አካላት ትስስር ትንተናና በውሃ ላይ የሚሰሩ ኢንቨስትመንቶች ከተቀናጀ
የውሃ ሃብት አስተዳደር ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን ዳሰሳ በማድረግ የዕቅዱ አካል ለማድረግ የሚያስችሉ ጉዳዮች በሚገባ ተመርምረው በርካታ ግብዓቶች ተወስደውበታል።
በመድረኩ ማጠቃለያም ዕቅዱን ከተግባር ጋር ማቆራኘትና ውጤታማ በማድረግ ማረጋገጥ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ብቻ የሚተው ሃላፊነት ባለመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ክፍተቶችና ስኬቶችን በጋራ ለመውሰድ መዘጋጀት እንዳለበት አቶ ደበበ ጥሪ ያስተላለፉ ሲሆን መርሃ ግብሩን በጋራ ያዘጋጀው የውሃና መሬት ሃብት ማዕከል በበኩሉ በዚህ ዙሪያ በርካታ ስራዎች እየሰራ መሆኑን በመጠቆም ወደፊትም በተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ዘርፍ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዕቅድን ለማሳካት ከቀድሞው በተሻለ ሁኔታ እንደሚሰራ የማዕከሉ የተፈጥሮ ሃብት አስተዳደርና የማህበራዊ ኢኮኖሚ ዘርፍ ዳይሬክተር ዶ/ር አማረ ባንቲደር አጠናክረው ገልጸዋል።