ኢትዮጵያ በውሃ ሃብት ልማት በሰራችው ሰፊ ስራ በርካታ ለውጦች ተመዝግበዋል - ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሃብታሙ ኢተፋ

ኢትዮጵያ በውሃ ሃብት ልማት በሰራችው ሰፊ ስራ በርካታ ለውጦች ተመዝግበዋል - ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሃብታሙ ኢተፋ   መጋቢት 1/2018 ዓ.ም(ው.ኢ.ሚ) የከርሰ ምድር ውሃ መረጃን በአግባቡ ለማስተዳደር በሚያስችሉ አጀንዳዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በካፒታል ሆቴል የምክክር መድረክ ተካሂዷል። የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ ከውሀ ጋር የተገናኙ ሠፊ አብዮታዊ ስራዎች በማከናወኗ በርካታ ለውጦች ተመዝገቧል ብለዋል። ሀገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት ናት ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ፤ ከእነዚህ መካከል የከርሰ ምድር ውሃ ሃብት ትልቁ ጸጋ መሆኑን ጠቁመዋል።   የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሶስት ምሰሶዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሆነ ገልጸው፤ በኢነርጂ ልማት፣ በንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እና በውሃ ሃብት አስተዳደር እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል። የውሃ ሃብት አስተዳደር ዘርፍ በጣም አስፈላጊውና ለሁሉም የጀርባ አጥንት መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡ ውሃን ካላሰብን ስለኢነርጂ ማሰብ ያዳግታል፣ የውሃ ሃብትን ከግምት ውስጥ ካላስገባን ንጹህ መጠጥ ውሃን ማሰብ አንችልም ብለዋል።   ከዚህም ጋር ተያይዞም መስኖ ልማትን ማሰብ አይቀሬ ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ፤ የውሃ ሃብት አስተዳደር ዘርፉ ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ አመልክተዋል። የውሃ ሃብታችን ለብልጽግናችን መሰረት ነው ከሚለው ሃሳብ በመነሳትም ኢትዮጵያ ዛሬ በተለይ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ የተነሳ ትኩረትን የሳበችና ለዓለም አጀንዳ የሆነች ሃገር በመሆኗ ለሃይል አቅርቦት ዘርፉ የጎላ ድርሻ አላት ብለዋል፡፡   ክቡር ሚኒስትሩ ሀገሪቱ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን እውን ለማድረግ ወደ 48 ቢሊዮን የሚጠጋ ችግኝ መትከሏን አስታውሰዋል። የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድም አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውንና እነዚህ ውጤቶች ሁሉ የተገኙት ደግሞ ከውሃ ጋር የተገናኙ አብዮታዊ ስራዎችን በማከናወን በመሆኑ ልንኮራ ይገባናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡   በተለይም የከርሰ ምድር የውሃ ሃብትን በተቀናጀ አግባብ ለማስተዳደር የዘርፉን መረጃዎች በማዘመን በተደራጀ መንገድ መያዝ አስፈላጊ ነውም ብለዋል፡፡ በተለይም የግድቦችን መረጃዎችን በጥንቃቄና በአግባቡ ማስተዳደር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።   በመድረኩ የተገኙ ባለድርሻዎች ለከርሰ ምድር ውሃ አስተዳደር ዘርፉ መሳለጥ ግብዓት የሚሆን ሰፊ ሀሳብ አንስተዋል።

Share this Post