በተከዜ ተፋሰስ የፀባ-ዓይና ንዑስ ተፋሰስ የዳሰሳ ጥናትና የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ዕቅድ የባለድርሻ አካላት የግምገማ ዓውደጥናት እየተካሄደ ነው።
መቐለ፦ታህሳስ 20/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከውሃና መሬት ሀብት ማዕከል /WLRC/ ጋር በጋራ የሚተገበረውና የ BRIGHT ፕሮጀክት አካል በሆነው የተከዜ ቤዚን የፀባ-ዓይና ንዑስ ተፋሰስ ለማልማት በሚካሄደው የዳሰሳ ጥናትና የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ዕቅድ የግምገማ ዓውደጥናት ላይ ውይይት እየተደረገ ነው።
መድረኩን በይፋ ያስጀመሩት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ዶ/ር ሚካኤል መሀሪ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የውሃ ሀብት ተጠቃሚ የማድረግ፣ የማዳረስና የማስፋት ስራዎች እየተሰራ ነው ብለዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ የውሃ ሀብቱን ለመጠበቅ ከሚሰራባቸው አንዱ የBRIIGHT ፕሮጀክት ነው ያሉት ዶ/ር ሚካኤል ተፋሰስ ላይ የሚሰራ ስራ ለከተማም ሆነ ለገጠር መጠጥ ውሃ፣ ለኃይል አቅርቦትና ለተለያዩ አገልግሎት የሚውል ውሃን በአግባቡ ለመጠቀምና ለማስተዳደር ያግዛል ብለዋል።
ዶ/ር ሚካኤል አክለውም የውሃ ሀብት ስራ እንደመሰረተ ልማት ስራዎች በአንዴ ተሰርቶ የሚያበቃ ሳይሆን በዘላቂነት የሚሰራ በመሆኑ የተፋሰስ ተኮር ስራዎች በተቀናጀ መንገድ መመራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።
ከውይይቱ የሚነሱ ሀሳብ አስተያየቶች ጥሩ ግብዓት ስለሚሆኑ ሁሉም በንቃት እንዲሳተፉም ዶ/ር ሚካኤል አሳስበዋል።
የውሃና መሬት ሀብት ማዕከል ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጠና አላምረው በአምስት ቤዚኖች ላይ ተግባራዊ የሚያደርገው የ BRIGHT ፕሮጀክት ያለንን የውሃ ሀብት እንዴት ማስተዳደር እንደምንችል የሚያግዝ ነው ብለዋል።
በትግራይ ክልል ለሌሎች ቤዚኖች ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ተሰርቷል ያሉት ዶ/ር ጠና ፕሮጀክቱ በተከዜ ቤዚን የተመረጠው የፀባ-ዓይና ንዑስ ተፋሰስ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደ እምባ ጠባቂ እንዲኖር ለማድረግ ነው ብለዋል።
የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር አስተባባሪ ዶ/ር ብዙነህ አስፋው የተቀናጀ የውሃ ሀብትን ለማስፈን ከሚሰሩ በርካታ ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው የBRIGHT ፕሮጀክት በተከዜ ቤዚን ከተመረጠው የፀባ-ዓይና ንዑስ ተፋሰስ ሲሆን የተዘጋጀውን የነባራዊ ሁኔታ ዕቅድ ግምገማ ውይይት ላይ በሚገኘው ግብዓት በሳይንሳዊ መንገድ በመለየት በቅድሚያ ሊተገበሩ የሚችሉትን ለይቶ ወደ ስራ የምንገባበት ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ የአዋሽ፣ የአባይ፣ የስምጥ ሸለቆ፣ የኦሞ ጊቤ እና የተከዜ ቤዚኖችን በማልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በጥናት ላይ ተመስርቶ በቅንጅት የሚተገበር ነው ያሉት ዶ/ር ብዙነህ የውይይቱ አላማም ችግሮችን በሚገባ በማየት፣ ዋና ዋና ጉዳዮችን በቅደም ተከተል በማስቀመጥ በአጭር ጊዜ ተጨባጭ ለውጥ የምናመጣበትን አሰራር ተግባራዊ በማድረግ፤ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ቦታዎች ላይ ስራ እንዲሰራ ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።
በውይይቱ ከትግራይ ክልል፣ ከዞንና ከወረዳ የውሃና ኢነርጂ፣ የግብርናና የአካባቢ ጥበቃ ቢሮዎች፣ ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ ከትግራይ ግብርናና ጥናት ኢንስቲትዩት፣ ከውሃ ጥናትና ዲዛይን ኮንስትራክሽን፣ ከክልሉ የተመረጡ ቀበሌዎች የውሃ ተጠቃሚዎች፣ ከማህበረሰብ ተወካዮችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ሲሆን በቀጣይ ለተከታታይ ሶስት ቀናት ውይይት ይደረጋል።