የፀረ ኤች.አይ.ቪ /ኤድስ ቀንና የፀረ-ፆታዊ ጥቃት ቀንን ምክንያት በማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄደ።
ህዳር /2017 ዓ/ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራር እና ሰራተኞች የዓለም አቀፍ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ቀን እና የፀረ-ፆታዊ ጥቃት ቀንን ምክንያት በማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄደ።
የፀረ-ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ37ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ35ኛ ጊዜ "ሰብዓዊ መብትን ያከበረ የኤች አይ ቪ አገልግሎት ለሁሉም!" በሚል መሪ ቃል የተከበረ ሲሆን የፀረ-ፆታዊ ጥቃት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ33ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ19ኛ ጊዜ "የሴቷ ጥቃት የኔም ነው፤ ዝም አልልም!" በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች ተከበረ፡፡
መድረኩን ያስጀመሩት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ የውብዳር አሚኖ ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት በሴቶችና በህፃናት ላይ የሚፈፀም ማንኛውም ዓይነት አካላዊ፣ ወሲባዊ፣ ስነ-ልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር የሚያስከትል የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲሆን በሰላምም ሆነ በጦርነት ወቅት፣ በግልም ሆነ በማህበራዊ ህይወት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ከማሳደሩም በላይ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርስ ጥቃት በአእምሯዊና በአካላዊ ጤንነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር ነው ብለዋል።
ወ/ሮ የውብዳር አያይዘውም የበዓሉ ዋና ዓላማ የፀረ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን እና የፆታዊ ጥቃት ቀንን ምክንያት በማድረግ ለሚኒስቴር መ/ቤታችን አመራሮችና ሰራተኞች ግንዛቤ በመፍጠር ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በሽታን እና ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር በስራ ቦታዎች ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ በሚመለከት ግንዛቤ በማሳደግ የአመለካከትና የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ነው ብለዋል።
አክለውም ወንዶች በደረታቸው ላይ ነጭ ሪቫን የሚያደርጉት በሴቶች ላይ ማንኛውም አይነት ጥቃት ፈፅሞ ላለመፈፀምና ጥቃቱ በሌሎች ሲፈፀም ዝም ላለማለት ቃል የሚገቡበት መለያ ምልክት ነው ብለዋል።
የፀረ-ፆታዊ ጥቃት ቀን በማስመልከት የመወያያ ሰነድ ያቀረቡት ከኬር ኢትዮጰያ ወ/ሪት ረቂቅ መኮንን የፀረ-ፆታ ጥቃት ምንነትና ጥቃቱን ለመከላከል ማን ምን ኃላፊነት አለበት የሚለውን ሰነድ አቅርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያዊ ዘውዱ ኢኒሼቲቭ ጤና ማህበር አቶ ማቲዎስ አላሮ በኤች.አይ.ሺ/ኤድስ ዙሪያ ልምድ ያጋሩ ሲሆን ለጥያቄና መልስ ውድድር ተሳታፊዎች ከኬር ኢትዮጵያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።