የመጪው ክረምት ወቅት የአየር ጠባይ አዝማሚያ ትንበያ ይፋ ሆነ::

የ2022 ዓ.ም ክረምት ወቅት የአየር ጠባይ አዝማሚያ ትንበያ ይፋ ሆነ፡፡ በብሔራዊ ሜትርዎሎጂ ኢንስቲትዩትና አጋር አካላቱ በአዳማ ከተማ በተዘጋጀ ወርክሾፕ ላይ ከክረምቱ ወቅት የአየር ፀባይ አዝማሚያ ትንበያ በተጨማሪ ያለፈው በልግ ወቅት የአየር ጠባይ አዝማሚያ ትንበያ ከነባራዊው አየር ጠባይ ጋር የነበረው ተመሳስሎም ግምገማም ተካሂዷል፡፡ መድረኩን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ተገኝተው በንግግር የከፈቱት ሲሆን የአየር ጠባይ አዝማሚያ ትንበያ መረጃዎችን በፍጥነትና በስፋት ተደራሽ ማድረግ አስፈላጊና ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በጥር ወር የበልግ ወቅት የአየር ጠባይ አዝማሚያ ትንበያውን ኢኒስቲትዩቱ ይፋ ማድረጉን አስታውሰው በአብዛኛው ትንበያው ትክክለኛ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ የአየር ጠባይ አዝማሚያ ትንበያን ቀድሞ በመተንተን በዜጎች ሕይወትና ንብረት ላይ ሊደርስ የሚችልን ጉዳት መቀነስ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡ በቀጣዩ ክረምት የሚኖረውን የአየር ፀባይ አዝማሚያም በጥንቃቄ መመልከት እንደሚገባ ያሳሰቡት ክቡር ሚኒስትሩ የአየር ጠባይ አዝማሚያ ትንበያ መረጃዎችን በፍጥነትና በስፋት ተደራሽ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በበኩላቸው በተቋሙ ይፋ የሆነው የበልግ ወቅት የአየር ጠባይ ትንበያና አፈጻጸሙ በተደረገው ግምገማ እጅግ የተቀራረበ መሆኑን ገልጸው የመጪው ክረምት ወቅት የአየር ጠባይ አዝማሚ ትንበያ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ይፋ ለማድረግ መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ ኢንስትቲዩቱ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት የመጪዉ የ2014 ዓ.ም ክረምት ወቅት የአየር ጠባይ በትሮፒካል ፓስፍክ ውቅያኖስ የባህር ወለል ሙቀት በቀጣይ ወራቶችም ከመደበኛው በታች መቀዝቀዝ (ENSO-La-Nina) ተጽዕኖ ሥር ሆኖ እንደሚቀጥል፤ እንዲሁም የሰሜናዊ ህንድ ውቅያኖስ አሁን ያለው ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ የባህር ወለል ሙቀት መጠን (Neutral IOD) በቀጣዮቹ የክረምት ወራት (Negative IOD) እንደሚሆን የትንበያ መረጃዎች መግለጻቸውን አስረድተዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የወቅቱ ዝናብ አጀማመር በአብዛኛዉ መደበኛዉን ጊዜ ሊከተል እንደሚችልና በአወጣጥ ረገድ ግን ለተወሰኑ ቀናት ሊዘገይ እንደሚችል ተገልጿል፡፡ በዚሁ መሠረት የዘንድሮ የክረምት ወቅት ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸዉ በሆኑት የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸዉ ተጠቁሟል። በአጠቃላይ በመጪዉ የክረምት ወቅት የምዕራብ፣ የደቡብ ምዕራብ፣ የመካከለኛዉና የምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች በአብዛኛዉ መደበኛውን ዝናብ እንደሚያገኙ፤ የሰሜናዊ አጋማሽ አካባቢዎች ደግሞ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉ በትንበያው ተመላክቷል፡፡ በተጨማሪም የደቡብ የሀገሪቱ ቆላማ አካባቢዎች ከሚጠበቀዉ የላኒና ክስሰት ጋር በተያያዘ በወቅቱ መጨረሻ ወር ላይ ሊያገኙ የሚችሉት አነስተኛ መጠን ያለዉ ዝናብ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊኖረዉ ስለሚችል ከመደበኛዉ አንፃር ያነሰና ደረቅ ሆነዉ ሊቆዩ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዘዉ ህብረተሰቡ በሚቀጥሉት የክረምት ወቅት የሚጠበቀውን አመቺ የአየር ጠባይ ትንበያን ግምት ውስጥ በማስገባት በዚህ ወቅት የሚካሄደውን የግብርና እንቅስቃሴ ላይ ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥራዎችን ከባለሙያዎች ጋር በመመካከር በአግባቡ እንዲያከናውኑ እንዲሁም አልፎ አልፎ ከሚኖረዉ ከባድ ዝናብ ጋር በተያያዘ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑት ረባዳማና የወንዝ ዳር አካባቢዎች የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ሥራዎች ላይ ሊያደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ እንዲቻል አስፈላጊዉን የጥንቃቄ ስራ ከወዲሁ መከናወን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በመድረኩ ላይ የአየር ጠባይ አዝማሚያ ትንበያውን መሠረት በማድረግ በግብርና፣ በውሃ፣ በጤና፣ በኃይል ማመንጫዎች ዘርፍ ሊኖር የሚችለውን ተጽኖና አስተዋጽኦ በሚመለከት ትንተናዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

Share this Post