የ3ኛው የውሃና ኢነርጂ ሳምንት ኤግዚቢሽን የተማሪዎችን የምርምር እይታ እና ግንዛቤ የጨመረ ነው።
የ3ኛው የውሃና ኢነርጂ ሳምንት ኤግዚቢሽን የተማሪዎችን የምርምር እይታ እና ግንዛቤ የጨመረ ነው።
ጥቅምት 20/2019ዓም (ው.ኢ.ሚ)
በ3ኛው የውሃና ኢነርጂ ሳምንት ኤግዚቢሽን ላይ የተሳተፉ ተማሪዎች በዝግጅቱ ያዩአቸው የቴክኖሎጂና የምርምር ስራዎች የወደፊት የትምህርትና የምርምር አቅጣጫቸውን እንዲያሰፉ ትልቅ መነቃቃት እንደፈጠረላቸው ገለጹ።
በኤግዚቢሽኑ ላይ የተሳተፈው የምስራቅ ጎህ የሳይንስ ልህቀት ማእከል የ12ኛ ክፍል ተማሪ ክንድዬ ደረጀ እንደተናገረው ዝግጅቱ ከዚህ ቀደም የነበረውን ቲዮሪቲካል ግንዛቤ በተግባር ታግዞ በተሻለ ደረጃ እንዲረዳው አስችሎታል።
ኤግዚቢሽኑ የወደፊት የጥናትና ምርምር አቅጣጫዬን እንድቀይርና በውሃ ሀብት ዘርፍ ላይም ሰፊ የምርምር እድሎች እንዳሉ የተረዳሁበት ነው ሲል ገልጿል።
አክሎም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለወደፊት ምርምሮችና ጥናቶች የሚረዱ መረጃዎችንና አሰራሮችን በግልጽ ማሳየቱን በመጠቆም፣ በተለይም በሀገሪቱ የውሃ ሀብት ልማትና አስተዳደር ላይ እያከናወነ ያለው ስራ እጅግ ሊመሰገን የሚገባው መሆኑን አብራርቷል።
በሌላ በኩል ተማሪ ናፍቆት ኪዳኔ በበኩሏ፣ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ በሀይድሮ ፖሊቲክስ (Hydro-politics) የሚያከናውናቸውን ስራዎችና የነቃ የመደራደር አቅም ግንባታ እንቅስቃሴዎች በጥቅሉ ለመገንዘብ እንደቻለች ተናግራለች።
በተጨማሪም ሚኒስቴሩ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (IT) እና ዲጂታላይዜሽን ታግዞ የሚያከናውናቸው የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ አሰራሮች እጅግ ሳቢና ወቅታዊ ሆነው እንዳገኘቻቸው ገልጻለች።
በተመሳሳይ እቴጌ መነን የልጃገረዶች አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ኤግዚቢሽኑ ወጣቶችና ተማሪዎች በውሃ፣ በታዳሽ ኢነርጂ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላቸውን ፍላጎት ከማሳደጉም በላይ ለሀገር በቀል የምርምር ውጤቶችና ፈጠራዎች መጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።