የአባይ ተፋሰስን ለውሃ፣ ለኃይልና ለምግብ ዋስትና በሁለገብ ልማት ማልማት ወሳኝ መሆኑን ጥናት አመለከተ።
የአባይ ተፋሰስን ለውሃ፣ ለኃይልና ለምግብ ዋስትና በሁለገብ ልማት ማልማት ወሳኝ መሆኑን ጥናት አመለከተ።
አዲስ አበባ ጥቅምት 20/2019ዓ.ም
የአባይ ተፋሰስን በተቀናጀ የግድቦች ልማት፣ በውሃ ማከማቻና በመስኖ ልማት በማስፋፋት የኃይል ምርትን ለማሳደግ፣ የግብርና ምርታማነትን ለማሻሻልና የውሃ ሀብትን በተሻለ ሁኔታ ለመጠቀም ከፍተኛ አቅም እንዳለ በጥናት ተመላከተ።
በሦስተኛው የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት የቀረበው ጥናት፣ የአባይ ተፋሰስ ለውሃ፣ ለኃይልና ለምግብ ዋስትና በሚያበረክተው አስተዋጽኦ ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ በተፋሰሱ ውስጥ ያሉ ግድቦችን አጠቃቀም ከመስኖ ልማት ጋር በማቀናጀት የሚገኙ የልማት ዕድሎችን ተንትኗል።
ጥናቱን ያቀረቡት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሃይድሮሊክ ምህንድስና ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር አሰግድ ጋሻው፣ የአባይ ተፋሰስ ሰፊ የውሃና የመሬት ሀብት ቢኖረውም ሀብቱን በተቀናጀ መንገድ በማልማት የሚገኘውን ጥቅም ከፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።
በጥናቱ መሠረት፣ የአባይ ተፋሰስ በአካላዊ ሁኔታ እስከ 2.5 ሚሊዮን ሄክታር የሚደርስ የመስኖ ልማት አቅም እንዳለው ቢገመትም፣ በኢኮኖሚያዊ አዋጭነት ደረጃ ሊለማ የሚችለው አካባቢ 815 ሺህ ሄክታር ገደማ እንደሆነ ተመልክቷል።
ይህንን የመስኖ ልማት ለማስፋፋትም በዓመት 8.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ያህል ውሃ ሊያስፈልግ እንደሚችል ጥናቱ ያመለክታል።
በተመሳሳይ፣ በተፋሰሱ ውስጥ የሚገኙ የውሃ ማከማቻ ግድቦችን በተቀናጀ ሁኔታ በማልማትና በማስተዳደር ኃይል የማመንጨት አቅምን የበለጠ ማሳደግ እንደሚቻል ተጠቁሟል።
በተለይም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ከሌሎች ግድቦች ጋር በማቀናጀት የውሃ ፍሰትን መቆጣጠር፣ በደረቅ ወቅት የኃይል ምርትን ማረጋጋትና የኤሌክትሪክ አቅርቦትን የበለጠ ውጤታማ ማድረግ የሚያስችል መሆኑ ተብራርቷል።
የግድቦችን አሠራር ከመስኖ ልማት ጋር ማቀናጀት እንደሚያስፈልግም የጥናቱ ትንተና ያመለክታል።
በዚህም መሠረት የግድቦችን አሠራር በጋራ ማስተዳደር፣ የልማት ፕሮጀክቶችን በደረጃ ማስፈጸም፣ በተፋሰሱ ውስጥ የሚገኙ የውሃ፣ የኃይልና የግብርና ልማቶችን በተቀናጀ አሠራር ማስተሳሰር እንዲሁም የውሃ ሀብት አጠቃቀምን ለመወሰን የሚረዱ ዘመናዊ የውሳኔ ድጋፍ ሥርዓቶችን መጠቀም ከተጠቆሙት የመፍትሔ አቅጣጫዎች መካከል ይገኙበታል።
በአጠቃላይ፣ የአባይ ተፋሰስን በሁለገብና በተቀናጀ መንገድ ማልማት የኢትዮጵያን የኃይል ደህንነት ለማጠናከር፣ የመስኖ ግብርናን ለማስፋፋት፣ የምግብ ዋስትናን ለማሻሻልና ክልላዊ የኃይል ትስስርን ለማጎልበት ወሳኝ አቅም እንዳለው ጥናቱ አመልክቷል።