የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራሮችና የዘርፉ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር የሪፎርም ኮሚቴ አባላት እና አመራሮች በአርባ ምንጭ የልማት ፕሮጀክቶችንና የተፈጥሮ መስህቦችን ጎበኙ።
አርባ ምንጭ ፡ መስከረም 30/2019ዓ.ም
ለውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራሮችና የዘርፉን የመንግስት አገልግሎት አስተዳደር ሪፎርም የዝግጅት ሥራዎችን ሲያከናውኑ ለቆዩ የኮሚቴ አባላት የምስጋናና የማበረታቻ መርሃ ግብር አካል የሆነውን በአርባ ምንጭ ከተማ የሚገነባውን የፍሳሽ ዝቃጭ ማከሚያ ፕሮጀክት ጨምሮ የልማት ሥራዎችንና የከተማዋን የተፈጥሮ መስህቦች ጎበኙ።
በጉብኝቱ ወቅት በአርባ ምንጭ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው የፍሳሽ ዝቃጭ ማከሚያ ፕሮጀክት (Fecal Sludge Treatment Plant—FSTP) የግንባታ ሂደት፣ የፕሮጀክቱ አፈጻጸምና ለአካባቢ ጥበቃ ያለውን አስተዋጽኦ በተመለከተ የማብራሪያ ውይይት ተካሂዷል።
የሚኒስቴሩ የሳኒቴሽን መሰረተ ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኑረዲን ሙሀመድ እንዳብራሩት፣ ፕሮጀክቱ የፍሳሽ ዝቃጭን በአግባቡ በማከም የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ፣ የሕዝብ ጤናን ለመጠበቅና የታከመ ውሃን መልሶ ለመጠቀም የሚያስችል አሠራር ለመዘርጋት ያግዛል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በአገር በቀል ድርጅት በባይጌታ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እየተገነባ መሆኑንና አፈጻጸሙም 70 በመቶ መድረሱ ተገልጿል።
በ435 ሚሊዮን 658 ሺህ 753 ብር ወጪ እየተገነባ ያለው ፕሮጀክቱ የሁለት ዓመት የግንባታ ጊዜ የተመደበለት ሲሆን በታህሳስ ወር 2026 የማጠናቀቂያ ዕቅድ መኖሩ በቀረበው መረጃ ተመላክቷል።
የሚኒስቴሩ የሥራ አመራር ዋና ሥራ አስፈጻሚና የሪፎርሙ ዋና ኮሚቴ ጸሐፊ አቶ ኦልቀባ ባሼ እንደገለጹት፣ የምስጋናና የማበረታቻ መርሃ ግብሩ ባለፈው አንድ ዓመት የሪፎርሙን መሠረት የሚጥሉ ሰነዶችን ለማዘጋጀት የደከሙ የኮሚቴ አባላትን ጥረት ሙሉ በሙሉ ባይክስም፣ ሚኒስቴሩ ለሠሩት ሥራ ያለውን አክብሮትና እውቅና ለመግለጽ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
አቶ ኦልቀባ አክለውም፣ በመርሃ ግብሩ የልማት ፕሮጀክቶችን በመጎብኘት ተግባራዊ ተሞክሮ ለመቀመር፣ የሥራ አመለካከትን ለማጠናከርና በአዲስ መንፈስ በመነሳሳት ተቋሙን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
አመራሩና የሪፎርም ኮሚቴ አባላቱ ከፕሮጀክቱ ጉብኝት በተጨማሪ፣ የአርባ ምንጮችን፣ የአዞ ርባታ ማዕከሉንና የጋሞ ሕዝብን ባህላዊ እሴቶች የሚያሳዩ መስህቦችን ጎብኝተዋል።
ጉብኝቱ የአካባቢውን የልማት ተሞክሮ፣ ተፈጥሯዊ ሀብትና ባህላዊ እሴት ለመረዳት ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ነው አቶ ኦልቀባ የገለጹት።
በአጠቃላይ፣ መርሃ ግብሩ የሪፎርሙ የዝግጅት ምዕራፍ ውጤቶችን ወደ ተግባራዊ ለውጥ ለመቀየር፣ የተሻለ ቅንጅትና የጋራ ኃላፊነትን ለማጠናከር እንዲሁም በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የተሻለ አስተዳደርና ውጤታማ የሕዝብ አገልግሎት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር ያለመ ነውም ብለዋል።
የአርባ ምንጭ ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ላደረጉት አቀባበልም አቶ ኦልቀባ አመስግነዋል።
ስለተቋማችን ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት
ፌስቡክ
https://www.facebook.com/share/127Jeg3ch6p/
ቴሌግራም
http://t.me/mowieethiopia
ዌብሳይት
http://mowe.gov.et
X/ትዊተር
https://x.com/mowe_ethiopia
ዩቱዩብ
https://youtube.com/@ministryofwaterandenergy-e8842?s
ቲክቶክ
tiktok.com/@mowetikt