የቤዚን አቀፍ ዘላቂነት ማረጋገጫ ፕሮጀክት የትግበራ መነሻ ሪፖርት ግምገማ ተካሄደ

የቤዚን አቀፍ ዘላቂነት ማረጋገጫ ፕሮጀክት የትግበራ መነሻ ሪፖርት ግምገማ ተካሄደ ቢሾፍቱ፣ጳጉሜ 2 /2018 ዓ.ም.(ው.ኢ.ሚ) – በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ የሚተገበረው የቤዚን አቀፍ ዘላቂነት ማረጋገጫ (BaSRINET) ፕሮጀክት የትግበራ መነሻ ሪፖርት ግምገማ (inception report validation) ወርክሾፕ በፒራሚድ ሆቴል አካሂዷል። ፕሮጀክቱ ያካሄደው ወርክሾፕ የፕሮጀክቱን የትግበራ መነሻ ሪፖርት በጋራ መገምገም፣ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሙያዊ ግብዓት ማሰባሰብ፣ የታዩ ክፍተቶችን ማስተካከል እና ለቀጣይ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም የጋራ አቅጣጫ ማስቀመጥን ዓላማ ያደረገ መሆኑ ተመልክቷል ። በሚኒስቴሩ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ በመርሀግብሩ መክፈቻ ባደረጉት ንግግር፣ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ለውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ቁልፍ የሥራ መስክ መሆኑን ገልጸዋል። አቶ ደበበ እንዳስገነዘቡት፣ የውሃ ሀብትን በዘላቂነት ለማልማትና በተገቢው ሁኔታ ለመጠቀም ተቋማትና የውሃ ተጠቃሚዎች በተቀናጀ አሠራር መሳተፍ እንዳለባቸው ጠቁመዋል። በዘርፉ የሚከናወኑ ዕቅዶችና ተግባራትም ከተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር መርሆዎችና ከሕጋዊ ማዕቀፎች ጋር የተጣጣሙ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ሞላ ረዳ በበኩላቸው፣ ፕሮጀክቱ የውሃ ሀብትን በተቀናጀና በዘላቂ መንገድ ለማልማትና ለመጠቀም የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል። የመነሻ ሪፖርቱ ግምገማም በፕሮጀክቱ ቀጣይ የሥራ እቅድ ላይ የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠርና ከባለሙያዎች የሚገኙ ምክረ ሀሳቦችን በማካተት የሥራውን ጥራት ለማሻሻል ወሳኝ ነው። በዚህ መድረክ የሚሰጡ ግብዓቶች በቀጣይ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም ወቅት የተሻለ ውጤት ለማስገኘት ያግዛሉ ብለዋል። በመድረኩ በዋናነት ፕሮጀክቱ በሶማሌ ክልል ቀላፎ ወረዳና በአፋር ክልል ያንጉዲ ወረዳ የሚያካሂደውን የተቀናጀ የውሃ ሀብት ልማት የሚመለከት የአዋጭነት ጥናት፣ ዝርዝር ዲዛይን እና የጨረታ ሰነድ ዝግጅት ያካተቱ የትግበራ መነሻ ሪፖርቶች በዘርፉ አማካሪዎች በዝርዝር ቀርበዋል። ተሳታፊዎችም በሪፓርቱ ላይ የተመሠረቱ ጥያቄዎችን አንስተው፣ ሙያዊ አስተያየትና ግብዓት ሰጥተዋል። የተነሱት ምክረ ሀሳቦች የጥናቱን አቅጣጫ ለማጠናከር፣ የተለዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል እና የዝርዝር ዲዛይንና የጨረታ ሰነድ ዝግጅቱ በተገቢው ጥራት እንዲከናወን ጠቃሚ መሠረት እንደሚፈጥሩ ተመልክቷል። በወረዳዎቹ የሚካሄደው የተቀናጀ የውሃ ሀብት ልማት ሥራ በአካባቢው ያሉ የውሃ ሀብቶችን በተገቢው ሁኔታ ለማልማትና ለተለያዩ የውሃ ተጠቃሚዎች ጥቅም እንዲያስገኙ ለማስቻል የሚያግዝ ተግባር መሆኑ ተጠቁሟል። በውይይቱ የተገኙ ግብዓቶችን በመጠቀም የትግበራ መነሻ ሪፖርቱን ማሻሻልና ማጠናከር፣ በቀጣይም በፕሮጀክቱ የታቀዱ ተግባራትን በተቀናጀና በዘላቂ አሠራር ለማስፈጸም የሚያስችሉ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡ ይጠበቃል። ስለተቋማችን ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ፌስቡክ https://www.facebook.com/share/127Jeg3ch6p/ ቴሌግራም http://t.me/mowieethiopia ዌብሳይት http://mowe.gov.et X/ትዊተር https://x.com/mowe_ethiopia ዩቱዩብ https://youtube.com/@ministryofwaterandenergy-e8842?s ቲክቶክ tiktok.com/@mowetik

Share this Post