በአሶሳ፣ በጋምቤላና በሰመራ-ሎጊያ ከተሞች የውሃ ብክነትን ለመቀነስና የፋይናንስ አቅምን ለማጠናከር የተዘጋጀው የመጨረሻ ሪፖርት ረቂቅ ተገመገመ

በአሶሳ፣ በጋምቤላና በሰመራ-ሎጊያ ከተሞች የውሃ ብክነትን ለመቀነስና የፋይናንስ አቅምን ለማጠናከር የተዘጋጀው የመጨረሻ ሪፖርት ረቂቅ ተገመገመ

አዲስ አበባ — ጥቅምት 27 ቀን 2019 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ)፦ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና የጣሊያኑ SWS Consulting Engineering አማካሪ ድርጅት በጋራ ባዘጋጁት የምክክር መድረክ፣ በሁለተኛው የከተማ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት (Second Urban Water Supply and Sanitation Project) ሥር በአሶሳ፣ በጋምቤላና በሰመራ-ሎጊያ ከተሞች የውሃ ተቋማትን የፋይናንስ አቅም ለማጠናከርና የውሃ ብክነትን ለመቀነስ የተዘጋጀው የመጨረሻ ሪፖርት ረቂቅ ተገምግሟል።

በአዲስ አበባ ጌትፋም ሆቴል በተካሄደው በዚህ የምክክር አውደ-ጥናት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሳኒቴሽን መሠረተ ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኑረዲን መሐመድ፣ አማካሪው ድርጅት ፕሮጀክቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በሦስቱ ከተሞች የተለያዩ ጥናቶችንና ምዘናዎችን በማካሄድ፣ በየሥራ ምዕራፉ የተለያዩ ውጤቶችንና ሰነዶችን ሲያዘጋጅ መቆየቱን ገልጸዋል።

የዕለቱ ውይይትም የሦስቱ ከተሞች ስትራቴጂዎችና ቢዝነስ ፕላኖች ተዘጋጅተው በመጠናቃቸው በተካሄዱት ጥናቶችና ምዘናዎች ውጤቶች ላይ ተመሥርቶ በተዘጋጀው የመጨረሻ ሪፖርት ረቂቅ ላይ የሚያተኩር የመጨረሻ የምክክር መድረክ መሆኑ ተመልክቷል።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሁለተኛ ከተሞች ፕሮጀክት ሲኒየር ኤሌክትሮሜካኒካል ስፔሻሊስት አቶ ታደሰ ከበደ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ በባንክ ፋይናንስ የሚደረግና በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚመራ መሆኑን ገልጸው ይህ የምክክር መድረክ የውሃ ብክነት ቅነሳ ስትራቴጂ (Reduction Strategy) እና የ10 ዓመት የቢዝነስ ፕላን ላይ በማተኮሩ በአማካሪው የተጠናበት የመጨረሻ ወርክሾፕ መሆኑንና የፕሮጀክቱ ዋና ትኩረት ገቢ የማይከፈልበትን የውሀ ምርት (Non-Revenue Water) መቀነስ ላይ በመሆኑ፣ ይህንን ተግባራዊ ማድረግ አዳዲስ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ከማስገንባት በላይ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በመድረኩ ከተሳታፊዎች የሚቀርቡ አስተያየቶችና ግብዓቶች በመጨረሻው ሪፖርት እንዲካተቱ እንደሚደረግና አማካሪው ድርጅትም በቀረቡት ግብዓቶች መሠረት ሪፖርቱን አሻሽሎ አጠናቆ እንደሚያቀርብ ተገልጿል። ከሪፖርቱ ዝግጅት መጠናቀቅ በኋላ ፕሮጀክቱ ወደ ቀጣዩ የትግበራ ምዕራፍ እንደሚሸጋገር ተገልጿል ።

በዕለቱ የSWS Consulting Engineering የጋራ ሥራ ማኅበር (JV) መሪና የፕሮጀክት ዳይሬክተር ኢንጂነር ጃንካርሎ ሲጋሪኒ (Engineer Giancarlo Cigarini) እና ሌሎች የአማካሪ ቡድኑ ባለሙያዎች በፕሮጀክቱ የተከናወኑ ጥናቶችን፣ ምዘናዎችንና የተዘጋጁ ስትራቴጂዎችን እንዲሁም የንግድ ሥራ ዕቅዶችን ውጤት ለተሳታፊዎች አቅርበዋል። በመቀጠልም የመጨረሻው ሪፖርት ረቂቅ ቀርቦ በይዘቱ፣ በጥናቱ ውጤቶችና በቀጣይ የትግበራ አቅጣጫዎች ላይ ሰፊ ውይይትና ግምገማ ተካሂዷል።

በውይይቱም በሦስቱ ከተሞች የሚገኙ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ተቋማትን የፋይናንስ አቅም ለማጠናከር፣ ያልተሰበሰበ ገቢንና የውሃ ብክነትን ለመቀነስ፣ የአሠራር ብቃትን ለማሳደግና ዘላቂ የውሃ አገልግሎትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ የጋራ ውይይት ተደርጓል።

በምክክር መድረኩ ላይ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተወከሉ ባለሙያዎች፣ የሁለተኛው የከተማ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት (2nd UWSSP) አስተባባሪዎች፣ የአሶሳ፣ የጋምቤላና የሰመራ-ሎጊያ ከተሞች የመጠጥ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል። በተጨማሪም የቴክኒክ መፍትሔዎችንና የጥናት ውጤቶችን ያቀረቡት የSWS፣ AI ENGINEERING፣ Hydroaid እና SMAT ኩባንያዎች የጋራ ሥራ ማኅበር (JV) ተወካዮችና ሌሎች ባለሙያዎችም በመድረኩ ተገኝተዋል።

የምክክር መድረኩ ዋና ዓላማ በጥናትና በምዘና የተገኙ ውጤቶችን በመጨረሻው ሪፖርት ማካተት፣ ሰነዱን በተሳታፊዎች የጋራ ግብዓት ማሻሻልና ለቀጣዩ የሙከራ ትግበራ እንዲሁም ለተጠናከረ ሥራ ጠንካራ መሠረት መጣል መሆኑ ተመላክቷል።

Share this Post