የአየር ንብረት ስጋትን በቅድመ-ጥንቃቄ መመከት፡ ለዘላቂ የውሃና ኢነርጂ ደህንነት!

የአየር ንብረት ስጋትን በቅድመ-ጥንቃቄ መመከት፡ ለዘላቂ የውሃና ኢነርጂ ደህንነት! መስከረም/15/2019 ዒ.ም (ው.ኢ.ሚ) የአየር ንብረት ተለዋዋጭነት፣ በተለይም ከኤል-ኒኖ ክስተቶች ጋር ተያይዞ የሚመጣው የሙቀት መጨመር፣ የዝናብ መዛባትና ድንገተኛ ከባድ ጎርፍ በግብርናው ላይ ብቻ ሳይሆን በውሃ አቅርቦትና በኃይል ማመንጫ መሠረተ-ልማቶቻችን ላይ ከፍተኛ ስጋት ይጋርጣል። አደጋ ከተከሰተ በኋላ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ቅድመ-ጥንቃቄ ማድረግና መረጃን መሠረት አድርጎ መዘጋጀት ተመራጭ መፍትሔ ነው። በመሆኑም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አደጋዎችን አስቀድሞ ለመከላከልና መሠረተ-ልማቶችን ለመጠበቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል። የድንገተኛ ከባድ ዝናብና የጎርፍ አደጋ የንፁህ መጠጥ ውሃ ማጣሪያ ጣቢያዎችንና የቧንቧ መስመሮችን እንዳያናጋ አስቀድሞ የመከላከያ ግንባታዎችን የማጠናከር፣ የውሃ ጥራትን በየጊዜው የመቆጣጠርና በድርቅ ወቅት የውሃ እጥረትን ለመቋቋም የዝናብ ውሃን የመሰብሰብ ሥርዓቶችን የማስፋፋት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። በኃይል ማመንጫ በኩልም የደለል ክምችትን ለመከላከል በግድቦች ዙሪያ የተፋሰስ ልማትን ማጠናከር፣ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች በንፋስና መሬት መንሸራተት እንዳይቋረጡ አስቀድሞ ፍተሻና ጥገና ማድረግ፣ እንዲሁም በውሃ ኃይል ላይ ብቻ ያለንን ጥገኝነት ለመቀነስ የፀሐይና የንፋስ ኃይል አማራጮችን አቀናጅቶ መጠቀም ወሳኝ ተግባራት ናቸው። ከብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት የሚሰጡ የአየር ሁኔታ ትንበያዎችንና የጥንቃቄ መልዕክቶችን በየአካባቢው ካለው የውሃና የኃይል አቅርቦት ሁኔታ ጋር በማገናኘት ወቅታዊ መረጃዎችን ለማኅበረሰቡ ማድረስ የአየር ንብረት ስጋትን ለመቀነስ ወሳኝ ሚና ስላለው፣ ትክክለኛ መረጃን በመጠቀም፣ የተፋሰስ ልማት ጥበቃን በማጠናከርና በቅድመ-ጥንቃቄ በመመራት የሰው ሕይወትንና የሀገርን ሀብት ከአደጋ በጋራ እንጠብቅ። ስለተቋማችን ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ፌስቡክ https://www.facebook.com/share/127Jeg3ch6p/ ቴሌግራም http://t.me/mowieethiopia ዌብሳይት http://mowe.gov.et X/ትዊተር https://x.com/mowe_ethiopia ዩቱዩብ https://youtube.com/@ministryofwaterandenergy-e8842?s ቲክቶክ tiktok.com/@mowetikto

Share this Post