9 ኪሎ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚችል የሶላር ፕሮጀክት ርክክብ ተደረገ።

9 ኪሎ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚችል የሶላር ፕሮጀክት ርክክብ ተደረገ።

ሚያዝያ 09/2016 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በወላይታ ዞን ነዋሴ 1ኛ ደረጀ ትምህርት ቤት 9 ኪሎ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚችል የሶላር ፕሮጀክት ርክክብ ተደረገ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ በርክክቡ ወቅት የሶላር ቴክኖሎጂው በትምህርት ቤቱ የሚገኙ የተማሪዎችን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትን እንደሚያሳድግ አመላክተው፤ በቀጣይም 1,400 በሚደርሱ የትምህርትና የጤና ተቋማት ውስጥ ቴክኖሎጂውን ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የሶላር ፕሮጀክቱ በደቡብ-ደቡብ ሦስትዮሽ ትብብር ፕሮጀክት አካል በሆነው የባዮ ማስ፣ የባዮ ጋዝ እና የሶላር ተጠቃሚነት ፕሮጀክት ሲሆን የኢፌዴሪ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የቻይና ንግድ ሚኒስቴርና የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ለሶላር ፕሮጀክቱ ግንባታ የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ፕሮጀክቱን በምርምር በማገዝ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልፀው፤

የፕሮጀክቱ ቀጣይነት እንዲረጋገጥ በዩኒቨርሲቲው ሥልጠናና ሙያዊ ድጋፍ የመስጠቱ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የነዋሴ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ በርገኔ በቀለ በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ በ2003 ዓ.ም በህብረተሰብ ተሳትፎ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸው፤ የሶላር ቴክኖሎጂው ከቅድመ መደበኛ እስከ 8ኛ ክፍል ለሚማሩ የነዋሴ ተማሪዎች የመማር ማስተማር ስራውን በከፍተኛ ደረጃ እያዘመነ መሆኑን ገልፀው፤ የተማሪዎቹን የመማር ፍላጎት እንደጨመረ መሄዱንና በዚህም ተማሪዎቹም ሆኑ መምህራን ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ሶላር ቴክኖሎጂው የሚያመነጨው 9 ኪሎ ዋት ኃይል የትምህርት ቤቱን ማህበረሰብ የመብራት ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ በተጨማሪ በትምህርት ቤቱ አቅራቢያ ለሚገኙ 30 አባዎራዎች የመብራት ችግር መፍታት የሚችል እንደሆነ ተገልጿል።

Share this Post