12ኛው የውሃና የውሃ ዲፕሎማሲ ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው።
ግንቦት 14/2017 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ያዘጋጀው 12ኛው የውሃና የውሃ ዲፕሎማሲ ኮንፈረንስ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ግቢ እየተካሄደ ነው።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በውይይት መድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር የውሃና ሀይድሮ ዲፕሎማሲ ኮንፈረንስ ኢትዮጵያ በውሃ ሀብቶቿ ዙሪያ ከዚህ በፊት የተፈጠሩ ትርክቶችን ማረም እና እውነታውን ለአለም ለማሳወቅ የዘርፉ ሙሁራን ተሰባስበው አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ታሳቢ በማድረግ መጀመሩን ጠቁመዋል።
ባለፉት ጊዜያት ከታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጋር በተያያዘ የነበሩ ተግዳሮቶች የውሃ ሀብታችንን የመጠቀም መብታችንን ይፈታተኑን እንደነበረም ገልጸዋል።
ክቡር ሚኒስትሩ ፎረሙ የውሃን ሳይንስን ከሚዲያና ዲፕሎማሲ ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ በርካታ ስራዎችን ለመስራት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ትኩረት የተሰጠ በመሆኑና ኢትዮጵያ ድንበርና ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብቶቿን በዘላቂነትና በሚፈለገው መጠን በማልማት ለመጠቀም የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም የትኩረት መስክ ነውም ብለዋል።
ከታችኞቹ የተፋሰስ ሀገራት ሊደርሱ የሚችሉትን ተፅዕኖዎች ተቋቁሞ ለማለፍና ሀገራችን ኢትዮጵያ ያሏትን የውሃ ሀብቶች አልምታ የመጠቀም መብቷን ለሌሎች ሀገራት ለማስረዳት ሚዲያውን መጠቀም አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኢ/ር ቦጋለ ገ/መድህን የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ባስተላለፋበት ወቅት ስለውሃ ሀብታችን ማወቅ ለሚፈልጉ ሀገራት ለማስረዳት የምርምር ተቋማትና ምሁራን ለፎረሙ ተጨማሪ አቅም በመሆናቸው ብሔራዊ ጥቅምን በሚያስገኘው ጉዳይ ላይ በትኩረት እየሰሩ ነው ብለዋል።
ውሃን ሁሉም ዜጋ የሚጠቀምበት አግባብ ቢለያይም በሀገራት መካከል የውሃ አጠቃቀምን ፍትሃዊ ለማድረግና የጋራ መግባባት እንዲኖር የውሃ ዲፕሎማሲና ኮሙኒኬሽን ፎረም ሚናው የላቀ ነው ብለዋል።
በመድረኩም የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ፣ በሚኒስትር ዴኤታ ማእረግ የሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ፤ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ክቡር ዶ/ር ኢ/ር አብደላ ከማልን እና የሕ/ተ/ም/ አባል ክቡር አቶ መሀመድ አልአሩሲን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው ምሁራንና ተመራማሪዎች፣ ተደራዳሪዎችና የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች እየተሳተፉ ነው።