የተደበቀው ሀይል (The hidden power) በሚል ርዕስ በሳይንስ ሙዚየም የተገነባው የውሃና ኢነርጂ ቋሚ ኤግዚቢሽን ሀገራችን ለመለወጥ ያለውን እምቅ አቅም ያሳያል ተባለ።
ሰኔ 10/2017ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተደበቀው ሀይል (The hidden power) በሚል ርዕስ በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም የገነባው የውሃና ኢነርጂ ቋሚ ኤግዚቢሽን ሀገራችን ለመለወጥ ያለውን እምቅ አቅም ያሳያል ተብሏል።
በሙዚየሙ ሲያስጎበኙ ያነጋገርናቸው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ ኤግዚቢሽኑ እንደ ሀገር ያሉን የውሃና ኢነርጂ እምቅ ሀብቶቻችን ሀገራችን ለመለወጥ ያላቸውን አቅም በተለይም ለታዳጊ ህጻናት በማሳየት ከወዲሁ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያስችላል ብለዋል።
ውሃ ከአፈጣጠሩ ጀምሮ እንዴት እንደሚታከም ፣ እንደሚጣራ እና ጥቅም ላይ እንደሚውል፣ ውሀን በቁጠባ እንዴት እንደምንጠቀም እንዲሁም የጎርፍ አደጋዎች የሚያደርሱትን ተጽእኖ በደንብ ለማስገንዘብ ኤግዚቢሽኑ ዲጅታላይዝ ሆኖ ቀርቧልም ብለዋል።
ኢነርጂን በማመንጨት ሂደት ያለውን እድገት አሁን እስከደረሰበት የእድገት ጎዳናን በሚያሳይ መልኩ የሀይድሮ ፣ ሶላር ፣ ጅኦተርማል ፣ የነፋስና የወደፊቱ የሃይድሮጂን ኢነርጅን እንዴት በተሻለ ሁኔታ ማመንጨት እንዳለብን ያሳያል ብለዋል።
የውሃና ኢነርጂ ኤግዚቢሽን ሞዴሎችን በመጠቀም መዘጋጀቱ ለየት እንደሚያደርገው የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው ውሃም ኢነርጅም ለተጠቃሚው እስከሚደርሱ የሚያልፉበትን ሂደት ከመመልከትና ከማዳመጥ ባለፈ ያለውን ስሜት በሚያሳይ መልኩ እንዲታይ ተደርጎ ቀርቧል ብለዋል።
ከሰኔ 6/2017ዓ.ም ጀምሮ ለእይታ ክፍት የሆነውን ኤግዚቢሽን በውጭም በሀገር ውስጥም ጎብኝዎች እየተጎበኘ መሆኑን የገለጹት አቶ ደበበ በሂደት የጎብኝዎችን አስተያየት እየተቀበልን ተጨማሪ ነገሮችን እናመቻቻለን ብለዋል።
ውሃም ሆነ ኢነርጂ የማይመለከተው እና የማይጠቀም አካል ስለሌለ የተዘጋጁት መረጃዎች በተለይም ለልጆች አዲስ እይታ እንዲኖራቸው ፣ ተመራማሪ እንዲሆኑ እና ሳይንስና ውሃ እንዴት እንደተገናኙ በደንብ የሚያዩበት በመሆኑ መጥተው ቢጎበኙ እንደ እንደትውልድም እንደ ሀገርም ተጠቃሚ የምንሆንበትን የውሃና ኢነርጂ ኤግዚቢሽን ገንብተናል ብለዋል።
የገጠር ኢነርጂ ቴክኖሎጅ ልማት ዴስክ ሀላፊ ወ/ሮ አለምነሽ ታረቀኝ ለአንድ ሀገር እድገት ወሳኝና መሠረት የሆነው የኢነርጂ ዘርፍ እንዴት እየዘመነ እንደመጣ እና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ እንደ ሀገር በአማራጭ ኢነርጂ ዘርፍ የተደረሰበት ደረጃ ህይወት ባለው መልኩ ለጎብኝዎች ቀርቧል ብለዋል።