የውሃ፣ ሳኒቴሽን እና ንፅህና አገልግሎት ስርዓትን ማጠናከር (SCRS WaSH) የቴክኒክ ድጋፍ ፕሮጀክት በስኬት መጠናቀቁ ተገለጸ።
ነሀሴ /2017ዓም(ው .ኢ .ሚ) በዩኒሴፍ እና በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኤምባሲ የገንዘብ ድጋፍ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የውሃ፣ ሳኒቴሽን እና ንፅህና አገልግሎት ስርዓትን ማጠናከር (SCRS WaSH) የቴክኒክ ድጋፍ ፕሮጀክት በስኬት መጠናቀቁ ተገለጸ።
በመርሀ ግብሩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ የውሃ፣ ሳኒቴሽን እና ንፅህና አገልግሎት ስርዓትን ማጠናከር (SCRS WaSH) የቴክኒክ ድጋፍ ፕሮጀክት ስኬታማ መሆኑ በዩናይትድ ኪንግደም መንግስት፣ በኢትዮጵያ መንግስት፣ በዩኒሴፍ እና በቁርጠኛ የክልል ባለድርሻ አካላት መካከል ያለውን ጠንካራ አጋርነት ያሳያል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘላቂ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የንጽህና አገልግሎት ተደራሽ ያደረገ ነውም ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በ18 ከተሞች የውሃ ብክነትን ከ11 በመቶ በላይ እንዲቀንስ ከማድረጉ ባሻገር የአሰራር ቅልጥፍናን እና የፋይናንስ ዘላቂነትን ማሻሻሉን ክቡር ሚኒስትር ዲኤታው ገልጸዋል።
የፕሮጀክቱ አስተዋፅኦ ከገቢ ውጭ ውሃን ለመቀነስ መንግስት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች ጋር ይጣጣማል፣ ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የፀሀይ ሀይል ውህደትን፣ የአቻ ትምህርት፣ አስተዳደርን በማጠናከር የውሃ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ለታለመላቸው አላማ መጠቀም፣ የመሠረተ ልማት መስፋፋት ፣ የተሻሻለ ቴክኒካል አቅም እንዲሁም በጠንካራ የአካባቢ ባለቤትነት የተደገፈ ተፅዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል።
በመጨረሻም የአየር ንብረትን የሚቋቋሙ የውሃ፣ የአካባቢ ጽዳትና የግል ንፅህና አገልግሎቶችን በማጠናከር ረገድ የምናደርገውን የጋራ ጥረት አስፈላጊነት እንደሚያሳይ በመግለጽ ለዚህ ተነሳሽነት ላደረጉት ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ የብሪቲሽ ኤምባሲ እንዲሁም ለዩኒሴፍ፣ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና ለክልል መንግስታት በአፈፃፀም ላሳዩት መሪነት ልዩ ምስጋና ይገባል ብለዋል።
ለሁሉም ተሳታፊዎች ፣ ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት ላበረከቱት ንቁ ተሳትፎም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
በመርሀ ግብሩ በፕሮጀክቱ ላይ የተገኙ ውጤቶች፣ያጋጠሙ ችግሮች ፣ግኝቶች እና ማጠቃለያ ጥናቶች ቀርበዋል።