የአባይ ተፋሰስ ዕቅድ ቴክኒካል ኦዲት እና የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር የሀብት ማፕንግ/resource mapping /ወርክሾፕ እየተካሄደ ነው።
ባህርዳር # ሚያዝያ 29/2018 ዓ/ም ውኢሚ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚተገበር በብራይት /BRIGHT /ፕሮጀክት የተዘጋጀ የአባይ ተፋሰስ ዕቅድ ቴክኒካል ኦዲት እና የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር የሀብት ማፕንግ/resource mapping / የባለድርሻ አካላት ወርክሾፕ ሌክአቬኑ ሆቴል እየተካሄደ ነው።
የአማራ ክልል የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ኢ/ር ዳኝነት ፋንታ በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው የአባይ ወንዝ 45 ሺህ ሜጋ ዋት የማመንጨት እና በሰፋፊ የመስኖ እርሻዎች ለማምረት የሚያስችል አቅም ያለው በመሆኑ ዕቅዶችን በመከለስ በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ያስፈልጋል ብለዋል።
የአባይ ተፋሰስ ከዚህ ቀደም በሙሉ አቅሙ ጥቅም ላይ እንዳይውል ያደረጉ ተግዳሮቶችን ቀርፎ የተሻለ ውጤት ለማምጣት የባለድርሻ አካላት ቅንጅትና ውይይት አስፈላጊ በመሆኑ የዕለቱ ወርክሾፕ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።
የአባይ ተፋሰስ አስተዳደር ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ዮሐንስ መላክ ከዚህ ቀደም የነበረው የአባይ ተፋሰስ ዕቅድ ወደ ትግበራ ምዕራፍ ለመግባትና ውጤት ለማምጣት አስቻይ ሁኔታ ጉድለትና የአሳታፊነት ክፍተት እንደነበረበት ተናግረዋል።
የተፋሰስ ዕቅዱን ክፍተትና ጉድለት ከባለድርሻ አካለት ጋር በመሆን በመገምገም ና ኦዲት በማድረግ ተጨባጭ በሆነ ሀብት ላይ የተመሠረተና አሳታፊ የሆነ የተከለሰ የተፋሰስ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ስለቀረበ ተሳታፊዎች ገንቢና ጠንካራ ሀሳብ በማቅረብ ዶክመንቱን ማዳበር ያስፈልጋል ብለዋል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የብሔራዊ የተቀናጀ ውሃ ሀብት አስተዳደር ፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር ብዙነህ አስፋው ውሃ የጋራ ሀብት በመሆኑ ከአንድ በላይ ክልሎች የሚጋሩት የውሃ ሀብት የጋራ ዕይታን ፣ቅንጅታዊ አሰራርን፣ አሳታፊነትን፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትንና የባለቤትነት ስሜት መፈጠር ስላለበት ዕቅዶችን መከለስ አስፈልጓል ብለዋል።
ደ/ር ብዙነህ የነበረው የተፋሰስ ዕቅድ ኦዲት ተደርጎ የተገኙ ክፍተቶች፣ የተከለሰው ዕቅድ ምን ምን ጉዳዮችን በዋናነት እንደሚይዝና ለተከለሰው ዕቅድ የትግበራ ምዕራፍ ምን አስቻይ ሁኔታዎች እንዳሉ የሚያሳይ ሰነድ ከሰፊ ገለፃ ጋር ለተሳታፊዎች አቅርበዋል።
በዕለቱ የአባይ ተፋሰስ አስተዳደር ዕቅድ ቴክኒካል ኦዲትና የክለሳ ሂደት በምን ጉዳዮች ላይ እንዳተኮረ በዘርፉ ባለሙያዎች በርካታ ሰነዶች ለተሳታፊዎች ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒሰቴር፣ ከአማራ፣ ከቤንሻንጉልና ከኦሮሚያ ክልሎች የውሃና ኢነርጂ፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ መሬት አስተዳደር፣ መስኖና የፕላን ቢሮዎች፣ ከአባይ ተፋሰስ አስተዳደር፣ ከብራይት /BRIGHT/ ፕሮጀክትና ከሌሎችም ተቋማት የዘርፉ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።