የሶስተኛው ምእራፍ ብሄራዊ የውሃ፣ ሳኒቴሽን እና ኃይጅን ፕሮግራም ስትራቴጂ እና ማስፈፀሚያ እቅድ (OWNP III – Strategy and Action Plan) ተገመገመ።

የሶስተኛው ምእራፍ ብሄራዊ የውሃ፣ ሳኒቴሽን እና ኃይጅን ፕሮግራም ስትራቴጂ እና ማስፈፀሚያ እቅድ (OWNP III – Strategy and Action Plan) ተገመገመ። ነሃሴ 7/2017 ዓ/ም (ው.ኢ.ሚ.ብ.ዋ.ማ) ላለፉት አመታት ሲፈፀም የቆየው ሁለተኛው ምእራፍ ብሄራዊ የመጠጥ ውሃ፣ ሳኒቴሽን እና ኃይጅን (OWNP-II) ፕሮግራም አፈፃፀም ግምገማ ውጤቶችን መሰረት በማድረግ የተዘጋጀው የሶስተኛው ምእራፍ ብሄራዊ የውሃ፣ ሳኒቴሽን እና ኃይጅን ፕሮግራም ስትራቴጂ እና ማስፈፀሚያ እቅድ (OWNP III – Strategy and Action Plan) ተገምግሟል። የግምገማ መድረኩን በንግግር የከፈቱት የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታው ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ፕሮግራሙ ከመተግበሩ በፊት ባሉት ዓመታት የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ማነስና የንፅህና አጠባበቅ ልምዶቻችን በሚፈለገው ደረጃ አለመሻሻል በርከት ያለው ህዝባችን መከላከል በሚቻሉ በሽታዎች ሲጠቃ የቆየ ሲሆን በቂ ካልሆነው አገልግሎት ባሻገር ፍትሃዊ አቅርቦት አለመኖር ችግሩን አሳሳቢ አድርጎት ቆይቷል ሲሉ ገልፀዋል፡፡ ክቡር አምባሳደር ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከአስር ዓመት በፊት የተቀረፀው የብሄራዊ የውሃ፣ ሳኒቴሽን እና ኃይጅን ፕሮግራም ልዩ ልዩ መተግበሪያ ዘዴዎችን በመከተል በርካታ ለውጦች ማስመዘገብ የቻለና በሌሎች ሃገራት ተሞክሮነት የሚጠቀስ መሆኑን አንስተዋል፡፡ በተጨማሪም ያለፉት ጊዚያት የፕሮግራሙ ውጤታማነት እንደተጠበቀ ሆኖ ያስቀመጥናቸውን እቅዶች ከማሳካትና ከአንድ ቋት ዋሽ ፕሮግራም ተግባራት ውጭ ያሉ አፈፃፀሞችን ከማቀናጀት አንፃር ያሉብንን ተግዳሮቶች ሊመልስ የሚችል በርካታ አካላት የተሳተፉበት እና ሁሉንም የሀገሪቱ ወረዳዎችና የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚያደርግ የሶስተኛው ምእራፍ ብሄራዊ የውሃ፣ ሳኒቴሽን እና ኃይጅን ፕሮግራም ስትራቴጂ እና ማስፈፀሚያ እቅድ (OWNP III – Strategy and Action Plan) የተዘጋጀ በመሆኑ ይህ መድረክ ተጨማሪ ግብዓት ለማካተት ያለመ ስለሆነ ሁሉም ተሳታፊ የሚጠበቅበትን ተሳትፎ ማድረግ ይገባል ብለዋል። የሶስተኛው ምእራፍ ስትራቴጂ እና ማስፈፀሚያ እቅድ በዮኒሴፍ ገንዘብ ድጋፍ እዮሪካ አማካሪ በተባለ ድርጅት የተዘጋጀ ሲሆን የድርጅቱ አማካሪ አቶ ከበደ ፋሪስ የሶስተኛውን ምእራፍ አጠቃላይ የዝግጅት ሂደቶችን፤ በሁለተኛው ምእራፍ የታዩ ክፍተቶችን እና ሶስተኛው ምእራፍ ላይ የተቀመጡ አዳዲስ ሃሳቦችን በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን አቶ አስራት ጌታነህ ደግሞ የፕሮግራሙን አጠቃላይ የፊዚካልና ፋይናንስ እቅድ አቅርበዋል፡፡ በመድረኩ ፈፃሚ ሚኒስትር መ/ቤት አመራሮች፤ የልማት አጋሮች፤ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጀቶች፤ የሚኒስትር መ/ቤቱ የሚመለከታቸው ባለሙያዎችና ፕሮግራም ዩኒት አስተባባሪዎች፤ የግል ሴክተር ተወካዮችና የምርምር ተቋማት ተገኝተው አስተያየት የሰጡ ሲሆን በተሳታፊዎች በኩል የሶስተኛው ምእራፍ ዶክመንት በሚገባ የዳበረና ተቋማዊ አደረጃጀት ማጠናከርን ጨምሮ በርካታ አዳዲስ ጉዳዮችን ያካተተ መሆኑን በጥንካሬ በማንሳት የውስጥ አቅምን በሚገባ ከመጠቅም፤ የአመራር የጎላ ተሳትፎ ከማጠናከር፤ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ከማሳተፍ፤ የግሉ ዘርፍ የነቃ ተሳትፎን ከማረጋገጥ፤ የውጭ ሀብት ምንጭ የሆኑ አካላትን የልማት ፍላጎት ከማገናዘብ እና የፀሃይ ሃይልን ከመጠቀም ጋር በተያያዘ ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ በአማካሪ ድርጅቱ በኩል በተሳታፊዎች ለቀረቡት ጥያቄዎችና ሃሳቦች ምላሽ በመሰጠት ዎርክ ሾፑን በመሩት ሚ/ር ካቡካ ባንዳ ከዩኒሴፍ እና የብሄራዊ ዋሽ ማስተባበሪያ ፅ/ቤት አስተባባሪው አቶ አብይ ግርማ በኩል ሁሉም ተሳታፊዎች ሃሳብና አስተያየቶቻቸውን በማካፈላቸውና የአማካሪ ድርጅቱ ተወካዮች ላቀረቡት ገለፃ አመስግነው ሰነዱ በቀጣይ የተነሱ ገንቢ ሃሳቦችን አካቶ እንደሚዘጋጅ በመግለፅ መድረኩ ተጠናቋል፡፡

Share this Post