ሁለተኛው ምዕራፍ ብሄራዊ የአንድ ቋት የመጠጥ ውሃ፣ ሳኒቴሽን እና ኃይጅን ፕሮግራም (OWNP-CWA II) የ2017 ዓ/ም አፈፃፀምን በመገምገም የፕሮግራሙን የ2018 ዓ/ም እቅድ አፀደቀ።
ሃምሌ 10/2017 ዓ/ም (ው.ኢ.ሚ.ብ.ዋ.ማ)
ፕሮግራሙን በበላይነት የሚመራው ስትሪንግ ኮሚቴ በ16 ኛው ስብሰባው የ2017 ዓ/ም አፈፃፀምን ጨምሮ እስከ አሁን በፕሮግራሙ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተከናወኑ የብሄራዊ የመጠጥ ውሃ ሳኒቴሽን እና ኃይጅን አፈፃፀሞችን የገመገመ ሲሆን የፕሮግራሙን የ2018 በጀት ዓመት እቅድም አፅድቋል፡፡
የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ እና የስቲሪንግ ኮሚቴው ሰብሳቢ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ በመክፈቻ ንግግራቸው ባለፉት ዓመታት ንፁህ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በስትሪንግ ኮሚቴው ውሳኔ ሰጭነት እና በፈፃሚ መ/ቤቶች የተቀናጀ ርብርብ በ2017 ዓ/ም ውጤታማ ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን በቀጣይ ዓመትም ይህንን ለመድገም የሚያስችል እቅድ የተዘጋጀ በመሆኑ በሁሉም አካላት ዘንድ የጋራ ተደርጎ መፈፀም እንዲችል ለማፅደቅ ያለመ መድረክ መሆኑን አንስተዋል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የብሄራዊ ዋሽ ፕሮግራም አስተባባሪው አቶ አብይ ግርማ ከዚህ በፊት ስትሪንግ ኮሚቴው ውሳኔ ያሳለፈባቸው ጉዳዮችን፤ የ2017 ዓ/ም ተግባራት አፈፃፀም ሪፖርትንና የ2018 ዓ/ም ተግባራት እቅድ ከማስፈፀሚያ በጀቱ ጋር ለተሰብሳቢዎች አቀርበዋል፡፡
በሪፖርቱ ላይም የፕሮግራሙ ሁለተኛ ምዕራፍ መተግበር ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ በገጠር ንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት 1.53 ሚሊዮን ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ 2845 የውሃ ተቋማት መገንባታቸውን፤ የውሃ አገልግሎት አሰጣጥን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚያስቸሉ 2582 የዋሽ ኮሚቴዎች፤ 60 የውሃ ተቋማት ጥገና ሰጭ ማህበራት እና 51 የመለዋወጫ እቃዎች መሸጫ ሱቆች መከፈታቸውን ያመላከቱ ሲሆን 3 የመካከለኛና 17 አነስተኛ ከተሞች ውሃ ተቋማት መገንባታቸውን፤ 545 ትምህርት ቤቶችና 966 ጤና ተቋማት የተሟላ ዋሽ ፓኬጅ አገልግሎት ማግኘታቸውን እንዲሁም እስካሁን 2.3 ሚሊዮን ዜጎች በፕሮግራሙ ንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ተጠቃሚ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
በተጨማሪም ይህ OWNP-CWA II በመጠናቀቅ ሂደት ላይ የሚገኝ ሲሆን በቀጣይ በጀት ዓመት በሁሉም ክልሎች በፕሮግራሙ በታቀፉ ወረዳዎች ውስጥ የሚተገበሩ በርካታ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን በማንሳት ቀሪ የፕሮግራሙን ስራዎች ለማጠናቀቅ ከሚያስፈልገው በጀት ላይ ለ2018 በጀት ዓመት 18.47 ቢሊዮን ብር በእቅድ መቅረቡን እና የታቀዱ ስራዎችን በቅንጀት እና በከፍተኛ ቁርጠኝነት መስራት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።
በተሳታፊዎች በኩል የፕሮግራሙ አፈጻጸም በጣም ጥሩ መሆኑን እና ለሌሎች ፕሮጀክቶችም አልፎም ለሌሎች አገራትም ጭምር በምርጥ ተሞክሮነት መቅረብ የሚችል መሆኑን በማንሳት ንፁህ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት በሚለዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ የቻለ በመሆኑ ለጋራ ጥረቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የላቀ ተሳትፎ ጉልህ ድርሻ መኖሩን፤ የኮንትራከትር፤ ባለቤትና አማካሪ ሶስትዮሽ ስብሰባዎችን በማድረግ በቀሪ ጊዜያት ያልተጠናቀቁ ፕሮጀከቶችን ማጠናቀቅ እንደሚገባ፤ የክልሎች መቀናጆ በጀት ምደባ መጠናከር እንዳለበት፤ ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ክልሎች የተቀናጀ ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ፤ የግሉን ሴክተር ተሳትፎ ማጠናከር እንደሚገባ፤ በቀሪ ጊዜያት የሚፈፀሙ ስራዎችን ለማሳለጥና በፕሮግራሙ ሶስተኛ ፌዝ ግብዓትነት የሚያገለግሉ ምርጥ ተሞክሮዎች በልዩ ትኩረት መቀመር እንዳለባቸው ገልፀዋል።
የጤና ሚኒስትር ድኤታው ክቡር ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው ይህንን በዘርፈ ብዙ ሴክተሮች ቅንጅት የሚተገበር ሞዴል ፕሮግራም የተለያዩ ሃገራት ልምድ ለመቀሰም የሚፈልጉት በመሆኑ ተሞክሮዎቹ መቀመር እንዳለባቸውና የበለጠ የአመራር ቅንጅት መኖር እንዳለበት በማንሳት ሁሉም ሚኒስቴር መ/ቤቶች አመራሮችና የልማት አጋሮች ተሳትፎ ለውጤታማነቱ ትልቅ ድርሻ እንደነበረው ገልፀዋል፡፡
ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ በማጠቃለያ ንግግራቸው በስትሪንግ ኮሚቴው ያልተቋረጠ አመራር፤ ከልማት አጋሮች ጋር በተቀናጀ መልኩ መሰራቱና ፈፃሚ አካላት ተግባራቸውን በሚገባ በመፈፀማቸው ያጋጠሙንን ችግሮች በመቅረፍ በውስን ጊዜያት ውጤታማነትን ማረጋገጥ መቻሉን ገልፀው በመድረኩ የተሰጡ ግብዓቶችን በማካተት በእቅዱ መሰረት ወደተግባር የሚገባ መሆኑን አቅጣጫ ሰጥተዋል።
በመርሃ ግብሩ የውሃና ኢነርጂ ፣የጤና፣ የትምህርት እና የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታዎች የተለያዩ የልማት አጋር ድርጅቶችና የፕ
ሮግራም ፈፃሚ ዩኒቶች በጋራ መክረዋል።
በመጨረሻም ስትሪንግ ኮሚቴው የፕሮግራሙን የ2018 ዓ/ም እቅድ በሙሉ ድምፅ በማፅደቅ ስብሰባውን አጠናቋል።