ከአለም አቀፍ ሶላር አሊያንስ (ISA) እና አጋር ድርጅቶች ጋር በትብብር የሚሰራው ስራ የኢትዮጵያን የኢነርጂ ሽግግር እንደሚያፋጥን ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ገለጹ፡፡

ከአለም አቀፍ ሶላር አሊያንስ (ISA) እና አጋር ድርጅቶች ጋር በትብብር የሚሰራው ስራ የኢትዮጵያን የኢነርጂ ሽግግር እንደሚያፋጥን ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ገለጹ፡፡ ነሃሴ 7/2017ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚነስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር/ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ከአለም አቀፍ ሶላር አሊያንስ (ISA) እና አጋር ድርጅቶች ጋር በትብብር የሚሰራው ስራ የኢትዮጵያን የኢነርጂ ሽግግር እንደሚያፋጥን፣ፈጠራን እንደሚያጎለብት እና ኢንቨስትመንቶችን እንደሚያበረታታ ገልጸዋል፡፡ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከአለም አቀፉ ሶላር አሊያንስ ጋር በጋራ በሚተገበሩ ጉዳዮች ላይ ለመምከር በተዘጋጀው መድረክ ንግግር ያደረጉት ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ በዋና ዳይሬክተር ሚስተር አሽሽ ካና ለሚመራው የዓለም አቀፍ የፀሐይ ኃይል አሊያንስ ከፍተኛ ደረጃ ተልዕኮ እና የአጋር ድርጅቶች ተወካዮችን በኢትዮጵያ መንግሥት ስም አመስግነዋል፡፡ ተልዕኮው የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት፣ የኢነርጂ ተደራሽነትን ለማጎልበት እና ፈጠራ እና ዘላቂ የኃይል አማራጮችን በመጠቀም የኢኮኖሚ እድገትን ለማሳደግ ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት ያሳያልም ብለዋል። በእለቱ የ400MW የሶላር ፓርክ ባለሶስትዮሽ ፕሮጀክት እና 700 ኪሎ ዋት ሶላር ሚኒ-ግሪድ ፕሮጄክት ውጥኖች ጨምሮ ቁልፍ የትብብር ስምምነቶች መፈረማቸው ኢትዮጵያ በፀሀይ ሀይል ለመጠቀም፣ የገጠር ኤሌክትሪፊኬሽንን ለማሻሻል ያላትን የማይናወጥ ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑንም ጭምር ነው ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት። በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ግቢ የ100 ኪሎ ዋት የሶላር ጣሪያ የመኪና ማቆሚያ ስራ መጀመሩ የታዳሽ ሀይል መፍትሄዎችን ከህዝብ መሠረተ ልማት ጋር በማዋሀድ ለግሉ ሴክተር እና ለማህበረሰቡ አርዓያ ለመሆን ቁርጠኝነትን ያሳያል ብለዋል። ኢትዮጵያ ለዘላቂ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር፣ የአካባቢ ማህበረሰቦችን የማብቃት እና የንፁህ ኢነርጂ ተጠቃሚነት ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን በተለይም በቂ አገልግሎት በሌለባቸው የገጠር አካባቢዎች እንዲዳረስስ ለማድረግ ቁርጠኛ ሆና እየሰራች ነውም ብለዋል፡፡ የሀገራችን ራዕይ በ2030 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴታው የዚህ ራዕይ እምብርት የሃይል አቅርቦት እንደመሆኑ የተትረፈረፈ የፀሐይ ኃይልን በመጠቀም የሀገር ውስጥ ፍላጎቶችን ከማሟላት ባሻገር ክልላዊ የኢነርጂ ማዕከል ለመሆን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ ከአለም አቀፉ ሶላር አሊያንስና አጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ እውቀት፣ ቴክኒካል ትብብር እና ስልታዊ አጋርነት ለኢትዮጵያ ፣ ለአፍሪካ ቀንድ እና ለሌሎችም ጭምር በሚጠቅም መልኩ ችግሮችን በመፍታት የፀሐይ ኃይልን በሙሉ አቅም በጠቀም እንደሚቻልም ገልጸዋል። አለም አቀፍ ሶላር አሊያንስ ዋና ዳይሬክተር ሚስተር አሽሽ ካና አለም አቀፉ የፀሀይ ሃይል ትብብር በተለያዩ መርሃ ግብሮች ዘላቂ የኢነርጂ ልማት ለማስፋፋት ከኢትዮጵያ ጋር በንቃት ሲሳተፍ መቆየቱን ጠቅሰው አጠቃላይ ግቡ የፀሐይ አፕሊኬሽኖችን በማስፋት፣ ተቋማዊ አቅምን በማሳደግ እና ለታዳሽ ሃይል ዝርጋታ ተስማሚ የቁጥጥር አካባቢን በማቋቋም ኢትዮጵያ ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ሀገራዊ ልማቶችን መደገፍ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

Share this Post