በባዘርኔት /BaSRINET/ ፕሮጀክት የሚተገበር የኢብሮ ሰዴን ማህበረሰብ ንዑስ ተፋሰስ ልማት ማስጀመሪያ መርሃግብር ተካሄደ።

በባዘርኔት /BaSRINET/ ፕሮጀክት የሚተገበር የኢብሮ ሰዴን ማህበረሰብ ንዑስ ተፋሰስ ልማት ማስጀመሪያ መርሃግብር ተካሄደ።   ባቢሌ # የካቲት 09/2018 ዓ/ም ውኢሚ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በባዘርኔት /BaSRINET/ ፕሮጀክት የሚተገበር በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሀረርጌ ዞን በባቢሌ ወረዳ የኢብሮ ሰዴን ማህበረሰብ ንዑስ ተፋሰስ ልማት ይፋዊ የተግባር ማስጀመሪያ መርሃግብር ተካሄዷል።   በማስጀመሪያ መርሃግብር ላይ የባቢሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኑሪ መሃመድ የለውጡ መንግስት እንደ ሀገር ትልልቅ ፕሮጀክቶችን እያቀደ በመተግበር ውጤታማ ስራ መስራቱን ጠቅሰው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ይህን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለውን ፕሮጀክ በወረዳችን እንድተገበር ዕድሉን ስለሰጠን በወረዳው ህዝብና በራሴ ስም አመሰግናለሁ ብለዋል። አቶ ኑሪ አክለው ፕሮጀክቱ ምንጮችን ከማጎልበት ፣አፈር እንዳይሸረሸርና የተራቆተ መሬት እንዲያገግም ከማድረግ አንፃር ከፍተኛ ጠቀሜታ ስላለው በባለቤትነት ስሜት እንዲሰሩና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የአካባቢውን ማህበረሰብ ከአደራ ጭምር ተማጽነዋል።   በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የባዘርኔት /BaSRINET/ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሞላ ረዳ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ፣በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን እና በኢነርጂው ዘርፍ ሰፋፊ ስራዎችን በመስራት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ ገልፀው ወደ ትግበራ ምዕራፍ የደረሰው የኢብሮ ሰዴን ማህበረሰብ ንዑስ ተፋሰስ ልማት ፕሮጀክት የስራው አንዱ አካል መሆኑን አብራርተዋል። አቶ ሞላ አያይዘው ፕሮጀክቱ የአርብቶ አደሩንና የከፊል አርብቶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል በተቀናጀ የልማትስራ፣በመስኖ፣በመጠጥ ውሃ፣ በሶላር ኢነርጂ ፣የአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራዎችን በመስራት የሚተገበር መሆኑን ገልፀው በትግበራው ውጤት ለማምጣት የህብረተሰቡ ቁርጠኝነት ወሳኝና የግድ እንደሆነ ተናግረዋል።   በዕለቱ በትግበራው ላይ ለሚሳተፉና ስራውን ለሚያሳልጡ የአካባቢው ነዋሪዎች የአተገባበር ስልት ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በዘርፉ ባለሙያዎች ተሰጥቷል። ቤዚን አቀፍ ዘላቂነት ማረጋገጫ BaSRINET ፕሮጀክት በአምስት ኮምፖነንቶች ለይ ትኩረት አድርጎ የሚተገበር ሲሆን የዕለቱ መርሃግብር አንዱና የዝግጅት ምዕራፍ ተጠናቆ የኢብሮ ሰዴን ማህበረሰብ ንዑስ ተፋሰስ ልማት ወደ ትግበራ የማስገባትና ስራ ማስጀመሪያ ምዕራፍ መሆኑ ተገልጿል።

Share this Post