ከ839 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት አለኝታ ልየታና ልማት የመጠጥ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ውል ስምምነት ተፈረመ፡፡
ህዳር 12/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በመተማና ሁመራ አካባቢዎች የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት አለኝታ ልየታና ልማት 14 የመጠጥ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ስራዎችን ለማከናወን ከ 839 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጭ የውል ስምምነት ፈርሟል፡፡
ስምምነቱን የፈረሙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ ፕሮጀክቱ የምስራቅ አፍሪካ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት አካል ሲሆን በ240 ቀናት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ገልጸዋል፡፡
የፕሮጀክቱን ውል የወሰደው የውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን በገባው የውል ስምምነት መሰረት ስራውን በጥራት ፣በሚጠበቀው የጊዜ ገደብ እና በሚፈለገው አግባብ በማከናወን የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባው ክቡር አቶ ሞቱማ አሳስበዋል፡፡
የውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዘመነ ጸሀይ ከ2015ዓ.ም ጀምሮ በደቡብ አካባቢ በተለያዩ ቦታዎች 34 የመጠጥ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ስራዎችን በወሰዱት ውል መሰረት በጥሩ አፈጻጸም ማጠናቀቃቸውን ገልጸው አጣየ፣ ሸዋሮቢት ፣ሞጣና መካነሰላም አካባዎች ደግሞ በተመሳሳይ መልኩ ውል ወስደው ወደ ስራ መግባታቸውን ነግረውናል፡፡
ስራ አስፈጻሚው አክለውም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህንን እድል ስለሰጣቸው በማመስገን በ2015 እና 2016 ዓ.ም ያሳዩትን ጥሩ አፈጻጸም በማጠናከር በገቡት ውል መሰረት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሀላፊነታቸውን በሚገባ እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል፡፡