የአሳይታ አፋምቦ የመጠጥ ዉሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ከ52 ሽህ በላይ የአካባቢው ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገለጸ፡፡

የአሳይታ አፋምቦ የመጠጥ ዉሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ከ52 ሽህ በላይ የአካባቢው ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገለጸ፡፡ ሀምሌ 23/2017 ዓ.ም. (ው.ኢሚ.) በቀጣይ ሳምንታት ኮሚሽኒንግ ስራው የሚጀምረው የአሳይታ አፋምቦ የመጠጥ ዉሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ከ52 ሽህ በላይ የአካባቢው ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገለጸ፡፡ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ በቀጣይ ሳምንት የመስመር ፍተሻ ስራዎች የሚጀመሩለት የአሳይታ አፋምቦ የመጠጥ ዉሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ከ52 ሽህ በላይ የአካባቢው ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ የፊዚካል ስራው፤ በተለይ የግንባታ እና የኤሌክትሮ ሜካኒካ ስራው ተጠናቋል ያሉት ክቡር አምባሳደሩ፤ በቀጣይ የመስመር ሙከራውን ማከናወን እንዲሁም የውሃ አገልግሎት ተቋሙን ማደራጀት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡ ብቁ የሆነ መዋቅር ማደራጅትና አገልግሎት አሰጣጡን በብቃት መመምራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ የአካባቢው ማህበረሰብም መሰረተልማቱን በመጠበቅና በመንከባከብ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የውሃ አገልግሎት ተቋሙን በማደራጀት ሂደት ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ድጋፍ እንደሚያርግም ጠቁመዋል፡፡ ከ72 ኪ.ሜ. በላይ የተለያየ መጠን ያላቸው ፓይፖች የተዘረጉለት ፕሮጀክት፤ 31 ቦኖዎች በቀበሌዎች የተገነቡ ሲሆን፤ 12 ቦኖዎች ደግሞ በትምህርትና በጤና ተቋማት መገንባታቸው ተጠቁሟል፡፡ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት ተጠቁሟል፡፡ የግንበታ ስራውን ወገሬት ኮንስትራክሽን ያከናወነ ሲሆን፤ የማማከር ስራውን የአፋር ዲዛይንና ቁጥጥር ኢንተርፕራይዝ አከናውኗል፡፡ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በተመራው የመስክ ጉብኝት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት አመራሮችን ጨምሮ የክልሉ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡

Share this Post