ከ5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የተገነባው የንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ።
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ቦረና ዞን የመዳ ወላቡ ወረዳ ቢዲሬ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለተጠቃሚዎች ክፍት ሆነ።
ህዳር 7/2018ዓ.ም (ውኢሚ) በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ውሃ ላይ ያሉ ትልቁ ስኬታችን ጉድጓድ ተቆፍሮ ውሃ ሲወጣ እና ፕሮጀክቱ ህይወት ዘርቶ ወደ ህብረተሰቡ ሲደርስ ነው በማለት የወረዳው ነዋሪዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
ስራ ሲሰራ ከእውቀት ጎን ለጎን ፋይናስ አስፈላጊ ነው ለዚህም መንግስታችን የህዝባችንን ኑሮ ለማሻሻል መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ፣ከአለም ባንክ፣ከአፍሪካ ልማት ባንክ ከዩኒሴፍ ፣ከፊደራልና ከክልል መንግስት በሚገኝ ገንዘብ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከዚህ ቡሀላ ፕሮጀክቱ ወደ ውሃ አገልግሎት የሚተላለፍ በመሆኑ የወረዳው የውሃ አገልግሎት ተረክቦ ሲያስተዳድር ህብረተሰቡ በታሪፋ መሠረት በመክፈል አገልግሎቱ እንዲጠናከር ማድረግ ግዴታ ነው በማለት ክቡር አምባሳደር አስፋው አሳስበዋል ።
በወረዳው 4 የጤና ተቋማት 9 ትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት ያጠናቀቀና 4 ጉድጓዶች 54.9 ኪ.ሜ የቧንቧ መስመር 22.7 ኪ.ሜ ማስተላለፊያ እና 32.2 ኪ.ሜ ማከፋፈያ አውታር 3 የአገልግሎት ማጠራቀሚያዎች ያሉትና 12 የሕዝብ ምንጮች እና 2 የከብት ገንዳዎ ተሰርተው ለተቃሚ ክፍት መሆናቸውንም ሚኒስትር ዲኤታው ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢ/ር ሚሊዮን በቀለ በበኩላቸው ወረዳዋ በብዙ የማህበራዊ አገልግሎት ላይ ከፍተኛ ችግሮች ያሉባት ሲሆን ወደ 75% የሚሆነው የወረዳው ዝቅተኛ መሬት በመሆኑ በተደጋጋሚ ድርቅ እና ወረርሽኝ የበሽታ ተለይቶ የሚታወቅ ነው ይህም ደህንነቱ የተጠበቀ የውሃ እና የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽነት አስፈላጊ ያደርገዋል ብለዋል።
ኢንጅነር ሚሊዮን በማያያዝ ፕሮጀክቱ ጠንካራ እና የበለጸጉ ማህበረሰቦችን ለመፍጠር የጤና፣ የኢኮኖሚ ልማት፣ ትምህርት እና ማህበራዊ ችግሮችን ይቀርፋል ብለዋል ።
ፕሮጀክቱ 36,073 ቢድሬ ከተማ ነዋሪዎችና 3 የሳተላይት መንደሮች ተጠቃሚ ያደርጋል።
የፕሮጀክቱ የገንዘብ ምንጭ ዩኒሴፍ (KfW)፡ 4.16 ሚሊዮን ዶላር ከመንግሥት 1.23 ሚሊዮን ዶላር ባጠቃላይ በ5.38 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተገንብቷል።
በመርሀ ግብሩ ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዳኤታዎች፣የዩኒሴፍ ተወካዮች ፣የኦሮሚያ ክልል ውሃ እና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ፣የወረዳው አመራሮች እና ነዋሪዎች ተገኝተዋል።