በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ35ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ መሆናቸው ተገለጸ።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ35ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ መሆናቸው ተገለጸ። ነሃሴ 14/2017ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) ውሃና ኢርጂ ሚኒስቴር ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በጋራ ሲተገበር በቆየው የአረንጓዴ አየር ንብረት ፈንድ ፕሮጀክት (GCF project ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ35ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ አድርጓል ተብሏል። በክልልሉ የዚህ እድል ተጠቃሚ በሆነው የማርቆ ልዩ ወረዳ ሰሜን ቆሸ ቀበሌ የተገነባውን የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከየክልሎቹ የመጡ የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች ጎብኝተውታል። በስፍራው ያነጋገርናቸው በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአረንጓዴ አየር ንብረት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ጌትነት ፈጠነ ፕሮጀክቱ ድሬዳዋ አስተዳደርን ጨምሮ በ9ክልሎች በ22 ወረዳዎች የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት ላለፉት 5ዓመታት ተግባራዊ ተደርጎ በርካታ የህብረተሠብ ክፍሎችን የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ የቻለ ነው ብለዋል። በፕሮጀክቱ በውሃው ዘርፍ ምንጭ በማጎልበት ፣ የጥልቅና የመካከለኛ የውሃ ጉድጓዶችን በመቆፈር የህብረተሠቡን የመጠጥ ውሃ ችግር በመፍታት ረገድ ትልቅ ስራ ተሰርቷል፤ ለዚህ ደግሞ የማርቆ ልዩ ወረዳ ማሳያ ነው ብለዋል። የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የውሃ መስኖና ማዕድን ቢሮ የአረንጓዴ አየር ንብረት ፈንድ ፕሮጀክት ተ/አስተባባሪ አቶ ክፍሌ ቱልሞ በፕሮጀክቱ ክልሉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ከ35 ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ በክልሉ ውሃ አጠር በሆኑ አካባቢዎች በርካታ ችግሮችን ያቃለለ ከመሆኑ ባሻገር የሴቶችን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያም ከ17ሺ በላይ ሴቶች የእድሉ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል። የማርቆ አካባቢ በፍሎራይድ የተጠቃ መሆኑ ችግሩን አባብሶት እንደነበር የጠቀሱት ተ/ አስተባባሪው ውሃው በፍሎራይድ ትሪትመንት እየታከመ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ብለዋል። ስራ ተሰራ የሚባለው ዘላቂ አገልግሎት ሲሰጥ ነው ያሉት ተ/አስተባባሪው የተገነቡ የውሃ ተቋማትን ህብረተሰቡ እንዴት መጠበቅና መንከባከብ እንዳለበት ከፍተኛ የማነቃቃት ስራም ተሰርቷል ብለዋል። ከዚህም ባሻገር ህብረተሰቡን ወደ ክፍያ ስርዓት ለማስገባት የሚያስችል በየተቋማቱ የዋሽ እና የፌደሬሽን ኮሚቴ የማደራጀት ስራ እንደተሰራም ነው የገለጹት። ጎን ለጎንም በበጋ ወቅት ከመጠጥነት የሚተርፈውን ውሃ መስኖ በማልማት የህብረተሰቡን የንሮ ደረጃ ለማሻሻል ከፍተኛ አበርክቶ ያለው ፕሮጀክት ነው ብለዋል። ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርንና እና ገንዘብ ሚኒስቴርን በተጠቃሚው ማህበረሰብ ስም አመስግነዋል። የማርቆ ልዩ ወረዳ የGCF አስተባባሪ አቶ ምትኩ ሂሳቦ በበኩላቸው የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን ችግር ለመቀነስ ተኩረት አድረጎ የሚሰራው የአረንጓዴ አየር ንብረት ፈንድ ፕሮጀክት እንደ ወረዳ ትልቁና አንገብጋቢ የሆነውን የመጠጥ ውሃ ችግር ፈትቶልናል ብለዋል። በአምስት አመቱ የፕሮጀክቱ ትግበራ እንደ ወረዳ 14ሺ የህብረተሰብ ክፍሎችን የንጹህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ አድርጎልናል ብለዋል። ቀሪ ስራዎችንም ክልልሉ ፣ ዞኑና ወረዳው ከማህበረሰቡ ጋር በጋራ ተግባራዊ እንደሚደረጉ ያላቸውን እምነት በመግለጽ የተገነቡት የውሃ ተቋማት ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ማህበረሰቡ በንቃት መጠበቅ አለበት ብለዋል።

Share this Post