ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ የመሩት ቡድን የ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖን ጎበኙ።

ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ የመሩት ቡድን የ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖን ጎበኙ። አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳንቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ የተመራ ቡድን፣ የ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖን ጎብኝቷል። በጉብኝቱ ላይ የሚኒስቴሩ አመራሮችና የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አመራሮች ተሳትፈዋል። ኤክስፖው በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተዘጋጀ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን ማስተዋወቅ፣ ኢንዱስትሪዎችን ማጠናከር እና የኢትዮጵያን ምርት ማበረታታት ዋና ዓላማው ነው። በተጨማሪም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና የፈጠራ ስራዎችን ለማስተዋወቅ አስፈላጊ መድረክ መሆኑ ተገልጿል። ኤክስፖው ለአገር በቀል ፋብሪካዎች ምርታቸውን ለህዝብና ለገበያ ማቅረብ ዕድል ከመፍጠሩ ባለፈ፣ ኢንቨስተሮች፣ አምራቾች እና ገዥዎች እንዲገናኙ ያግዛል ተብሏል። በጉብኝቱ ወቅት ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ እንደገለጹት በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ከ70 በመቶ በላይ የውሃ ግንባታ ማቴሪያሎች በውጭ ምንዛሬ ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ እነዚህን በአገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው አመልክተዋል። የአገር ውስጥ ምርት መጠቀም እስከ 6 ወር የሚወስደውን የእቃ ግዥ ሂደትን በማፋጠን የግንባታ ጊዜንም በከፍተኛ ሁኔታ ያሳልጣል ብለዋል። በተጨማሪም የውጭ ምንዛሬን በመቀነስ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ጉልህ መሆኑን ገልጸዋል። ቀደም ሲል በውጭ ላይ ጥገኛ የነበረው ቴክኖሎጂ በአገራችን መመረቱ ትልቅ ጅማሮ ነው፤ ይህንን ማበረታታት ይገባል ብለዋል። እንዲሁም የአገር ሀብትን ወደ ስራ መቀየር ከፍተኛ ጠቃሚነት እንዳለው በመግለጽ፣ እንደ ኤክስፖው ያሉ መድረኮች አይኖቻችንን ወደ አገር ውስጥ ምርት ማዞር እንዳለብን ግንዛቤ የሚፈጥሩ መሆናቸውን አክለዋል። በአጠቃላይ ኤክስፖው የኢትዮጵያን ኢንዱስትሪ በማሳደግ ኢኮኖሚውን ለማጠናከር እና የአገር ውስጥ ምርት ጥራትን ለማሻሻል አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል። በኤክስፖው ላይ ከመንግስትና ከመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ከአለም አቀፍና ከአገር በቀል የንግድ ተሳታፊዎች ተሳትፈው ቴክኖሎጂያቸውን እያስተዋወቁ መሆኑ ተገልጿል።

Share this Post