የሁለተኛው ምእራፍ የአንድ ቋት ብሄራዊ የውሃ፣ ሳኒቴሽን እና ኃይጅን ፕሮግራም (OWNP - CWA II) የ2017 ዓ.ም አፈፃፀም እና የ2018 ዓ.ም እቅድ ትውውቅ መድረክ ተካሄደ።
ነሃሴ 9/2017 ዓ/ም (ውኢሚ/ብዋማ) የሁለተኛው ምእራፍ የአንድ ቋት ብሄራዊ የመጠጥ ውሃ፣ ሳኒቴሽን እና ኃይጅን (OWNP-CWA II) ፕሮግራም የ2017 ዓ.ም አፈፃፀምና የ2018 ዓ.ም እቅድ ትውውቅ መድረክ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች፥ ስራ አስፈፃሚዎች፥ የክልል ቢሮ ሃላፊዎች፥ የልማት አጋር ድርጅቶች፥ የፌደራልና ክልል ፐሮግራም ፈፃሚ ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት በሃዋሳ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ በመክፈቻ ንግግራቸው የፕሮግራሙ ስትሪንግ ኮሚቴ ውሳኔዎችን መሰረት በማድረግ የ2017 ዓ/ም በፌደራልና ክልል አመራሮችና ፈፃሚ አካላት ርብርብ ውጤታማ ተግባራትን የተከናወነበት ዓመት ሲሆን በተወሰኑ ክልሎች የመንግስት መቀናጆ በጀት (matching fund) አመዳደብ ውስንነት፥ አዲስ የተመሰረቱት የደቡብ ክልሎች አፈፃፀም ዝቅተኛ መሆን እና ተገቢውን የፕሮግራም ሰው ሃይል ምደባ ላይ የታዮትን ክፍተቶች መሙላት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ክቡር አምባሳደር በቀጣይ የማስፈፀም አቅማችን በማጠናከር ፕሮግራሙን በቀሪው ጊዜ መፈፀም በመግለፅ የፕሮግራሙ ሶስተኛው ምእራፍ ዝግጅት እየተከናወነ ሲሆን የህዝብ ቁጥር በመጨመሩ ምክንያት ማሟላት ያለብን ተጨማሪ ፍላጎት መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ በ2030 እ.ኤ.አ ላይ የተያዙ የልማት ግቦችንና የሀገራችን አስር ዓመት የልማት እቅድ ታሳቢ ያደረጉ ስራዎችን በቀሪ አጭር ጊዜያት ለመፈፀም የሚያስችልና የመፈፀም አቅምን የሚያጠናክር ለየት ያለ አሰራር የሚከተል ምእራፍ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በግምገማ መድረኩ የብሄራዊ ዋሽ ፕሮግራም ማስተባበሪያ፤ የውሃ ፕሮግራም ማኔጅመንት ዩኒት እና የተመረጡ ክልሎች ሪፖርት ቀርቧል፡፡
የብሄራዊ ዋሽ ፕሮግራም ማስተባበሪያ ፅ/ቤት አስተባባሪው አቶ አብይ ግርማ የስትሪንግ ኮሚቴው ውሳኔ ሃሳቦችን፤ የ2017 ዓ/ም ተግባራት አፈፃፀም ሪፖርትንና ለፕሮግራሙ በጸደቀው 18.5 ቢሊዬን ብር በ2018 ዓ/ም የሚከናወኑ ተግባራትን እቅድ ያቀረቡ ሲሆን የውሃ ፕሮግራም ማኔጅመንት ዩኒት ሪፖርት ደግሞ በአቶ ታሪኩ አብዲሳ ቀርቧል፡፡ በሁሉም ክልሎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው መከናወን የሚገባቸው የጨረታ ሂደት ላይ ያሉትን ጨምሮ በግንባታ ላይ ያሉ መጠናቀቅ ያለባቸው ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ፤ ዘላቂ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በትኩረት መሰራት እንዳለበት፤ የአካባቢና ማህበራዊ ጥበቃ ተግባራት ቅድሚያ መሰጠት እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡
በተሳታፊዎች በኩል በርካታ የውይይት አጀንዳዎችን በማንሳት የሁለተኛው ምእራፍ ከመጠናቀቁ በፊት በተለይ በ2018 በጀት ዓመት ወደ ኋላ የቀሩትን በማጠናቀቅና የፕሮጀክት አፈፃፀምን በማሳደግ የፕሮግራሙን ቀሪ ጊዜያት ለዶክመንት ማደራጀት ስራን ማዋል እንደሚገባ ሃሳብ ተሰጥቷል፡፡
የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ሚኒስትር ድኤታ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ የቀረንን ውስን ጊዜ ያገናዘበ የተግባር ተሳትፎ የሚያስፈልግ መሆኑን፤ የመረጃ አስተዳደርን ማጠናከር ልዩ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት፤ የሪፖርት መናበብን ማስተካከል እንደሚያስፈልግ፤ የፕሮጀክቶች ክትትልን በክሳስተር ድጋፍ ማድረጉ መቀጠል እንዳለበት ያነሱ ሲሆን ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ በበኩላቸው የሰላም ችግር ቢገጥማቸውም ውጤታማ መሆን የቻሉ ክልሎች መኖራቸው መልካም መሆኑን እና የበጀት ችግር የገጠማቸውን ፕሮጀክቶች ሚኒስቴር መ/ቤቱ መፍትሄ ለመስጠት የሚጠበቅበትን መስራቱን በመግለፅ የቀረበውን የቀጣይ በጀት ዓመት እቅድ የጋራ በማድረግ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባ አቅጣጫ በመስጠት የቀኑ ውሎ የተጠናቀቀ ሲሆን በሚቀጥሉት ቀናት የሪፖርትና መረጃ አያያዝ ስርዓትን ለማጠናክር የሚያስችል ስልጠና እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡