ከፈረንጆቹ 2013 ጀምሮ እየተተገበረ የሚገኘው የናሽናል ዋን ዋሽ ፕሮግራም ሁለተኛውን ምእራፍ በማጠናቀቅ ሶስተኛውን ምእራፍ ለመጀመር የሚያስችል የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡

መጋቢት 4/2016 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከፈረንጆቹ 2013 ጀምሮ እየተተገበረ የሚገኘው የናሽናል ዋን ዋሽ ፕሮግራም ሁለተኛውን ምእራፍ በማጠናቀቅ ሶስተኛውን ምእራፍ ለመጀመር የሚያስችል የውይይት መድረክ በዋሽንግተን ሆቴል ተካሂዷል፡፡

በእለቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር አስፋ ዲንጋሞ መንግስት ለዜጎች ንጹህ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎትን በፍሃዊነትና በዘላቂነት ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ እና ይህንን እውን ለማድረግም ፖሊሲና ስትራቴጅ ተቀርጾ በመተግበር ላይ መሆኑን ግልጸዋል፡፡

በናሽናል ዋን ዋሽ ፕሮግራም በምእራፍ አንድና ሁለት የትግበራ ሂደት በንጹህ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አቅርቦት ላይ የተሻለ ውጤት መጥቷል ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በሁለቱ ምዕራፎች ከ10 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን በንጹህ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት ተጠቃሚ ከመሆናቸው በተጨማሪ ወጥ የሆነ የአሰራር ስርዓት እንዲፈጠር፣ በዋን ዋሽ ሴክተርና በልማት አጋር ድርጅች መካከል ያለውን ትስስርና ትብብር በማጠናከር ረገድም ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል፡፡

የዋን ዋሽ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ አብይ ግርማ እንደገለጹት በፈረንጆቹ 2025 ሶስተኛው ምእራፍ የዋን ዋሽ ፕሮግራም ለማስጀመር ታላሚ ያደረገ ውይይት እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው ባለፉት ሁለት ምእራፎች የፕሮጀክት አፈጻጸም የታዩትን ክፍተቶች በመለየት በተለይም የሚገነቡ የውሃ ተቋማት ቀጣይነት ባለው መልኩ አገልሎት እንዲሰጡ ህረተሰቡም በባለቤትነት ስሜት ይዞ እያስጠገነ እንዲጠቀም ለማድረግ ትኩረት ተደርጎ የሚሰራበት ምእራፍ ነው ብለዋል፡፡

እንደ አስተባባሪው ገለጻ በተለይም በድርቅና ጎርፍ በተደጋጋሚ የሚጠቁ አካባቢዎችን ዘላቂነት ባለው መልኩ በንጹህ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ተጠቃሚ ለማደረግ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራና አዲስ የውሃ ተቋማትን መገንባት ብቻ ሳይሆን ከአሁን በፊት የተገነቡትም ቀጣይነት ባለው መልኩ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ አቅም ግንባታ ላይ ትኩረት ተደርጎ ለመስራት ታላሚ ያደረገ ውይይት ነው ብለዋል፡፡

የውሃና ሳኒቴሽን ስራ የሁሉንም ህረተሰብ ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ መንግስት በሰጠው ትኩረት ልክ ህብረተሰቡ ውሃን በእንክብካቤ ፣በቁጠባና በንጽህና ይዞ እንዲጠቀም ሲሉም አስተባባሪው መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡

በእለቱ ከአለም ባንክ ፣ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ከጤና ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር እንዲሁም ከክልል ውሃና ኢነርጂ፣ጤና፣ ትምህርትና ፋይናንስ ቢሮች የመጡ ከፍተኛ አመራሮች ተሳታፊ ነበሩ፡፡

Share this Post